የቤተሰብ ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት

የቤተሰብ ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት

በአስፋው አማረ

በኢትዮጵያ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የተጀመረው ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ነው፡፡ በ1952 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሪቱ የሕግ አካል ሆኖ ተደነገገ፡፡ ይሁንና ላለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ደረጃውን ያሟላ የኩነቶች የምዝገባ ሥርዓት በአገሪቱ ተግባራዊ እንዳልተደረገ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡

መንግሥት የዜጎች የመረጃ ምዝገባ ሥርዓትን ዕውን ለማድረግ ይቻል ዘንድ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ 760/2004 እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 278/2005 መነሻ በማድረግ የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲዎችን በማቋቋም ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡

በአገሪቱ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሥርዓት እውን እንዲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት ልማት ፈንድ (ዩኒሴፍ) የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡

የዓለም አቀፍ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አሠራር መርህን የተከተለ ዘመናዊ የወሳኝ ኩነት የአመዘጋገብ ሥርዓት ለማከናወን የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍም ሆነ የአሠራር ሥርዓት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልነበረም፡፡

አገሪቱም የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሟሟላትና ምዝገባው የሚሰጠውን ጠቀሜታ ከማረጋገጥ አንፃር ከፍተኛ ክፍተት ነበረበት፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በመንግሥታዊ አስተዳደር ተቋማት፣ በተለይም በከተማ አስተዳደሮች ወጥነት በሌለው መመሪያ ላይ በመመሥረት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ደረጃውን ባልጠበቀና በተበታተነ ሁኔታ ምዝገባው ሲከናወን ቆይቷል፡፡

ይህም በየጊዜው ሊዘጋጁ የሚገባቸው የሕዝብ ብዛትና ምጣኔ እንዲሁም ወሳኝ የማኅበራዊና የልማት መለኪያዎች በአግባቡ እንዳይከናወኑ አድርጓል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ፥ የሲዳማ ክልል እየሰራ ያለውን ተሞክሮ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡

የሲዳማ ብሐራዊ ክልላዊ መንግስት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የቤተሰብ ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎትን በይፋ መጀመርን አስመልክቶ ባሳለፍነው ሳምንት የንቅናቄ መድረክ ተካሂዶ ነበር።

ከየካቲት 18/2017 ዓ.ም ጀምሮ የቤተሰብ ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎትን በይፋ እንደተጀመረ ተጠቁሟል።

በንቅናቄ መድረክ ላይ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ ከዚህ ቀደም የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት ከሚታይባቸው አንዱ የሆነው የወሳኝ ኩነት ተቋም ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት መሰረታዊ ለውጥ ማስገኘቱን ተናግረዋል።

“በአንድ ተቋም አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን እርካታ ማስገኘት የተቻለ መሆኑን እና የነዋሪው ምዝገባን በተመለከተም የታወቀ፣ የተመዘገበና የዘመነ ማህበረሰብ ለመፍጠር በየደረጃው የሚሰራ ይሆናል” ብለዋል።

አቶ መኩሪያ አክለውም፥ ከሲዳማ ክልል ኤጀንሲ ጋር በቅንጅት በመስራት የተሞክሮ ማዕከል ለማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በበለጠ ተቋሙን ውጤታማ ማድረግ እንዲቻል ከተማ አስተዳደሩ ለቋሚ ቁሳቁስ፣ ለጽህፈት መሳሪያና ለሌሎችም ግዢዎች የሚሆን የ2 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ መንግስት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ተሰማ ጉዳዩን አስመልክቶ ሲናገሩ፦

“ዛሬ በአዲስ መልኩ ይፋ የተደረገው የቤተሰብ ምዝገባንና የነዋሪዎች አገልግሎት በፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ በወጣ አዋጅ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ የጸደቀ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በዚሁ ልክ በክልሉም በጸደቀው ደንብ መሰረት ወደ ስራ የተገባ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ታመነ፣ ሞዴል ከሆኑ ተቋማት መካከል ወሳኝ ኩነት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ምዝገባና በአዲስ መልኩ የሚሰጠው መታወቂያ ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከማስቻል በተጨማሪ ወንጀልን ለማስቀረትም የላቀ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።

በሐዋሳ ከተማ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት ማቴዎስ በበኩላቸው ሲያስረዱ፣ ይህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ2016 ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ገልጸዋል።

“በዚህም አገልግሎት በተገቢው መንገድ ህብረተሰቡን ማርካት እንደተቻለ እና የወሳኝ ኩነት የቤተሰብ ምዝገባ ለመንግስታዊ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳስገኘ አስረድተዋል።

በአንድ ማዕከል በሚሰጠው አገልግሎት አሁን ላይ በሰለጠኑ ባለሙያዎችና በዲጅታል በመታገዝ አንድ ሰው በ15 ደቂቃ አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል በማለት ተናግረዋል።

የክልሉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ የቤተሰብ ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ደመላሽ ደገፉ በንቅናቄ መድረኩ ላይ እንዳሳሰቡት ከሆነ፦

“ከዚህ በኋላ የሚሰጡ የትኞቹንም አገልግሎቶች ለማግኘት የቤተሰብ ምዝገባን ማከናወን የግድ ይሆናል” በማለት ተናግረዋል።

የንቅናቄ መድረክ ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው በተገኘው ውጤትና የአገልግሎት አሰጣጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ መደሰታቸውን ገልጸው፥ የቤተሰብ ምዝገባ ማከናወን የሰለጠነ ማህበረሰብና የስልጡን ከተማ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ማጠናቀቂያ ላይ ከዚህ በፊት የነበረውን መታወቂያ በመቀየር በአዲሱ የቤተሰብ ምዝገባ ዙሪያ የክልሉ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ እና የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ የውል ስምምነት ተፈራርመዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የኤጀንሲው የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ቀርቦ በስፋት ውይይት ተደርጎበታል።