የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ ከ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ከ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የዕቅዱን 89 በመቶ ማሳካቱን አስታወቀ፡፡

የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አሰባሰብ ከ 50 በመቶ በታች መሰብሰቡ ከዚህ በላይ ገቢ እንዳይገኝ እንቅፋት መሆኑም ተጠቁሟል።

መምሪያው የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና 2018 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት እያደረገ ነው።

የምክክር መድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ቶማስ ቶቤ ባለፈው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፍ ርብርብ በማድረግ በክልሉ ካሉ ዞኖች የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ 1ኛ ወጥተን ዋንጫ በማግኘታችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል ።

በመደበኛ እና በማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፥ በዚህም በአጠቃላይ 5 ቢሊዮን 114 ሚሊዮን 245 ሺህ 640 ተሰብስቧል ብለዋል።

በመደበኛ ገቢ ከ100 ፐርሰንት በላይ ማሳካት ቢቻልም በማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ከ50 በመቶ በታች በመፈፀሙ ከዚህ በላይ ገቢ እንዳይገኝ እንቅፋት መሆኑንም ገልጸዋል ።

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዞኑ ዋና አስተዳደሪ ዶ/ር ደምስ አድማሱ ዞናችን በርካታ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ችግር ያለበት ቢሆንም በአንፃሩ በተፈጥሮ ጸጋ ደግሞ በእጅጉ የታደለ መሆኑን ጠቁመው፥ ይህን የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ገቢ በመቀየር የዞኑን የልማት ጥማት ለማርካት የሁሉንም እርብርብ ይጠይቃል ብለዋል ።

ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ ካሉ ዞኖች 1ኛ ወጥተን ዋንጫ በማግኘታችን ሳንኩራራ በ2018 በጀት አመት ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰብ መስራት አለብን ነው ያሉት።

ከደረሰኝ አጠቃቀም እና ከሠራተኛ ስነ-ምግባር ጋር ተያይዞ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል ።

ዘጋቢ፡ አዕላፍ አዳሙ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን