በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ በሚል መርህ በሀገር ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘው ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ተገለጸ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ሴቶች ክንፍ አስተባባሪነት በአበሽጌ ወረዳ ቢዶ ቀበሌ “በጎነት ለኢትዮጽያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች የንቅናቄ መርሃግብር ተካሂዷል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የሴቶች ክንፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ፈለቀች ተክለማርያም፤ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መርህ በሀገር ደረጃ እየተተገበሩ የሚገኙ ሰው ተኮር ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረትን ይጠይቃሉ ብለዋል።
ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን ጉልበት፣ ገንዘብ እና እውቀትን በመጠቀምና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስጠቀም የኢትዮጵያ ብልጽግናን ለማሳካት ትልቅ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት።
ባለፉት 7 ዓመታት የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ በተሰሩ የክረምት የበጎ ፈቃድ ስራዎች አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ያሉት ዶ/ር ፈለቀች፤ በቀጣይም ብልጽግና ፓርቲ ያስቀመጠው ሰው ተኮር ተግባራትን በመከተል የመጪው ትውልድ አርዓያ መሆን ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል።
በተለይም እንደ ክልል ተለይተው ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች በትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካማ ቤት በመስራት፣ በአረንጓዴ አሻራና በቁጠባ ዘርፎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሄኖክ አብዱልሰመድ በበኩላቸው፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በቀጣይ ከሴቶች ክንፍ በተጨማሪ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ከ250 በላይ ለችግር የተጋለጡ ዜጎች መኖሪያ ቤት እንደሚሰራላቸው ገልጸዋል።
ሴቶች በጎነት ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው በመሆኑ ለማህበራዊ ብልጽግና ግንባታ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ሴቶች ክንፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሲቲ አብራር “በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል በብልጽግና ፓርቲ ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ ስራ ንቅናቄ እንደ ጉራጌ ዞንም ሁሉም የዞኑ መዋቅር የሴቶች ክንፍ በተገኙበት ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።
በመርሃ-ግብሩ ማስጀመሪያ በአበሽጌ ወረዳ ቢዶ ቀበሌ ለአንዲት አቅመ ደካማ ለሆኑ እናት ለቤት ግንባታ የሚውል ድጋፍ በማድረግ፣ የአረንጓዴ አሻራ በማኖርና የተለያዩ የሴቶች ማህበራት ልማት ስራዎች የመስክ ምልከታ በማድረግ ወደ ተግባር ተገብቷል።
በዘርፉ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አበክረው እንደሚሰሩ በማከል በጎነትን ባህል በማድረግ ረገድ ማህበረሰቡ ያለውን የመተጋገዝ ልምል ማጠናከር አለበት ሲሉ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ አዱኛ ትዛዙ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የዲላ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም እና የ2018 ሥራ ፈላጊዎች ልየታ ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ
በጎፋ ዞን የደምባ ጎፋ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት የወረዳውን የ2018 ዕቅድ ማስፈፀሚያ በጀት ከ315 ሚሊዮን ብር በላይ አጸደቀ
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በተገቢ መደገፍና ማበረታታት ለሃገር ኢክኖሚ እድገት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተገለጸ