‎የዲላ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም እና የ2018 ሥራ ፈላጊዎች ልየታ ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ‎

‎የዲላ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም እና የ2018 ሥራ ፈላጊዎች ልየታ ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ‎

‎በ2018 በጀት ዓመት ከ12 ሺህ 7 መቶ በላይ ወጣቶችን ለይቶ ወደ ሥራ ለማሠማራት አቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ መምሪያው ገልጿል፡፡‎

‎የዲላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታሪኩ በየነ፤ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ላይ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ጉድለት ያለባቸውን ደግሞ በበጀት ዓመቱ ለማረም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ አብራርተዋል።‎

‎በ2017 በጀት ዓመት ለተለዩ ወጣቶች ሥልጠና ተሰጥቶ ግንዛቤ ከተፈጠረ ቦኋላ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሥራ ዕድል ተፈጥሯል ያሉት አቶ ታሪኩ፤ በጊዜያዊ ሥራ ላይ ከመቶ በላይ ተከናውኗል ብለዋል።‎

‎የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ተለውጠው ለሌሎችም ዕድል እንዲፈጥሩ ለማስቻል ሥልጠናውን ከሚሰጡ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።‎

‎በ2018 በጀት ዓመት ላይ 12 ሺህ 7 መቶ 76 ወጣቶችን የአካባቢውን ፀጋዎች መሠረት ባደረገ መልኩ በመለየት ወደ ሥራ በማሠማራት ተጠቃሚ ለማድረግ የንቅናቄ ሥራ መጀመራቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ተደራጅተው የቆጠቡት ወጣቶች ብድር ከዓለም ባንክ እና ሌሎች የግል ባንኮች እንደሚያገኙ ተናግረዋል።‎

‎በዚህ በጀት ዓመት የመንግሥታዊ ድጋፎች መካከል መሬት፣ ሼድ እና ሀብት ምደባን ጨምሮ ሌሎችን በአግባቡ ተደራሽ በማድረግ ወጣቶችን ከአነስተኛ ጀምሮ እስከ እንዱስትሪ ድረስ ለማጠናከር እንደሚሠራ ነው የገለጹት።‎

‎መድረኩን ያስጀመሩት የዲላ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ መንግሥቱ ተክሌ፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ማመቻቸት ለየትኛውም ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።‎

‎በተለይ ያሉ ፀጋዎችን በመለየት የሚገጥሙ ፈተናዎችን በማሸነፍ ከተሰራ በአጭር ጊዜ ወስጥ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በ2017 በጀት ዓመት ሥራ አፈፃፀም ላይ የተመዘገቡ ውጤቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።‎

‎ከአማረ አጥናፉ ቤተሰቦች ማህበር አቶ ፍሬ ዘለቀ እና ከዶሮ እርባታ ማህበር ደግሞ አቶ ምህረት ጌታቸው፤ ተደራጅተውና ጠንክረው በመሥራት የዋንጫና ሜዳልያ ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።‎

‎በቀጣይ ሥራቸውን አስፍተው ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተግተው እንዲሠሩ ሽልማቱ እንደሚያነሳሳቸው አስረድተዋል።‎

‎በመጨረሻም በከተማው ጥሩ በመንቀሳቅስ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እና ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ለተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የሜዳሊያ፣ የሰርተፊኬትና የዋንጫ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።‎

‎ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ጎበና – ከይርጋ ጨፌ ጣቢያችን