በጎፋ ዞን የደምባ ጎፋ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት የወረዳውን የ2018 ዕቅድ ማስፈፀሚያ በጀት ከ315 ሚሊዮን ብር በላይ አጸደቀ

በጎፋ ዞን የደምባ ጎፋ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት የወረዳውን የ2018 ዕቅድ ማስፈፀሚያ በጀት ከ315 ሚሊዮን ብር በላይ አጸደቀ

ምክር ቤቱ ባካሄደው 4ኛ ዙር መርሃ ግብር 12ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤው ልዩ ልዩ ሪፖርቶችንም አዳምጦ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

የደምባ ጎፋ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አበበ አማኔ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ ከፍተኛ የህዝብ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን ተልዕኮውም በህዝብ የነቃ ተሳትፎ ለወረዳው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ፋይዳ ያላቸውን ህጎችን በማውጣት አስፈፃሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው።

ምክትል አፈ ጉባኤዋ ወ/ሮ አዛለች ብላቴ የ2017 በጀት ዓመት የደምባ ጎፋ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤትን አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበው በአባላቱ ሀሳብና አስተያየት ተሰጥቶበታል።

ከዚህ ቀደም በሪፖርት የተመላከቱ የኦዲት ግኝቶችን ማስመለስ ዙሪያ የታዩ ውስንነቶች፣ የቋሚ ኮሚቴዎች ለተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍና ክትትል መጠናከር እንዲሁም ለቋሚ ኮሚቴዎች የተሠጡ ሥልጠናዎች በጠንካራ ጎን ተነስተው ምክር ቤቶች ወቅቱን ጠብቀው ጉባኤ ከማድረግ ረገድ የታዩ ጉድለቶች መታረም እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

የደምባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ አራታ የአስተዳደር ምክር ቤቱን ሪፖርት አቅርበው በምክር ቤቱ አባላት ሀሳብና አስተያየት ተሰጥቶበት በሙሉ ድምፅ ጸድቋል።

ምክር ቤቱ በ4ኛ ዙር መርሃ ግብር 12ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤው የ2018 በጀት 315 ሚሊየን 539 ሺህ 597 ብር እንዲሆን የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የወረዳው ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስራት አዳኝ የበጀት ረቂቁን እና በጀቱ የሚውልባቸውን የልማት መስኮች በዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በጀቱ በወረዳው ለሚካሄዱ ዘላቂ የልማት ግቦችና ለአስተዳደራዊ ተግባራት እንደሚውል ባቀረቡት የበጀት ረቂቅ አብራርተዋል።

የበጀቱ ምንጭ ከመንግሥት ካዝና፣ ከወረዳው ከሚሰበሰብ ገቢ፣ ከጤና እና ከትምህርት ተቋማት ገቢ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ፣ ከመንግሥት ከሚሰጥ ድጎማና ሌሎች ምንጮች ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በጀቱ ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም የነዋሪውን የልማት ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ ተግባራት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ምክር ቤቱም የቀረበለትን የከተማውን የ2018 ዕቅድ ማስፈፀሚያ በጀትም በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ዘጋቢ: ድጋፌ ድክሬ – ከሳውላ ጣቢያችን