“ስነጽሁፍ ላይ ያለኝን እውቀት ያመጣሁት በተመስጦ በማድመጥ ነው” – ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ

“ስነጽሁፍ ላይ ያለኝን እውቀት ያመጣሁት በተመስጦ በማድመጥ ነው” – ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ

በመሐሪ አድነው

የሳምንቱ እንግዳችን ጥበቡ በለጠ ይባላል፡፡ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ሲሆን ትውልድና እድገቱ ምን ይመስላል? አሁንስ ያለበት ደረጃ? ስንል አንስተን በአጠቃላይ የህይወት ተሞክሮው ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፤ አብራችሁን እንድትቆዩ ግብዣችን ነው፤ መልካም ንባብ፡፡

ንጋት:- በመጀመሪያ እንግዳችን ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆንክ በዝግጅት ክፍላችን ስም እጅግ እናመሰግናለን፡፡

ጋዜጠኛ ጥበቡ:- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት:- አስቀድመን ጨዋታችንን ጥበቡ በለጠ ማን ነው? ትውልድና እድገቱ ምን ይመስላል? ከሚለው እንጀምር፡፡

ጋዜጠኛ ጥበቡ:- ጥበቡ በለጠ የተወለደው ሚያዝያ 8/1966 ዓ.ም ከእናቱ ከወ/ሮ ወደርየለሽ ፋንታሁን እና ከአባቱ ከአቶ በለጠ ተፈራ ነው፡፡ ከዚህ ከሐዋሳ ወደ ሁለት መቶ ሃምሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው፣ የወርቅ ሀገር በሆነችውና እስከ 1937 ዓ.ም ድረስ አዶላ ተብላ በምትጠራው በኋላም በታዋቂው አርበኛ በደጃዝማች ከበደ ብዙነሽ ክብረመንግስት በተባለች ከተማ ነው፡፡

ንጋት:-  እድገትህ እንዴት ነበር?

ጋዜጠኛ ጥበቡ:- አራት ልጆች ቤት ውስጥ ይኑሩ እንጂ በርካታ የቤተ ዘመድ ልጆች በሚኖሩበት ቤት ያደኩኝ ሲሆን ወላጆቼም የተማሩ ነጋዴዎች ናቸው። በክብረ መንግስት ከተማ ጎንደር የተባለ ሆቴል ባለቤትም ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ እና በክብረ-መንግስት ቤት ስለነበራቸው ትምህርቴን በሁለቱም ከተሞች እየተዘዋወርኩኝ ነው የተማርኩት፡፡ በመዋእለ ህፃናት ፋንታ የቄስ ትምህርት ቤቱን ጨምሮ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል በራስ ብሩ ወልደገብርኤል የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት በክብረመንግስት ከተማ ተምሬያለሁ፡፡

የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁም ሰንደቅ ዓላማን የምሰቅል ተማሪዎችንም በሰልፍ ሰዓት ብሔራዊ መዝሙርን የማዘምርም ነበርኩኝ፤ በተጨማሪም በዚሁ ወቅት በአስደናቂ ሁኔታ ከሰርቶ አደር እና ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ዜናዎችን በማጠናቀር ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ለዚህ ሁሉ መነሻው የሆኑት እና ተፅዕኖ ያሳደሩብኝ የስፖርት ሳይንስ መምህሬ ለስነፅሁፍ ልዩ ፍላጎት እና ፍቅር የነበራቸው አጎቴ ድንበሩ ስዩም ናቸው፡፡ ከልጅነቴም በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበርኩኝ፡፡

የስድስተኛ ክፍል ትምህርቴን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በልደታ ሚሲዮን ትምህርት ቤት ተማርኩ፤ በመጀመሪያ ያነበብኩት ትልቅ መፅሀፍም አጎቴ ያመጣልኝን “እንደ ሠው በምድር እንደ አሳ በባህር” የሚል ርዕስ ያለውን የሩሲያ ትርጉም ነበር። ቀጥሎም ዛሬ በአማርኛ የስነፅሁፍ ታሪክ ትልልቅ የሚባሉ ልብወለድ መፃህፍትን ማንበብ ችያለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ የሁለት ከተሞች ወግ ነኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡

በክብረመንግስት እና በአዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜያት ትምህርቴን የተማርኩ ሲሆን  በንፋስ ስልክ ደግሞ ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ተምሬያለሁ፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጥሩ በሚባል ውጤት አልፌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባሁኝ፡፡

ንጋት:- ዩኒቨርሲቲ ስትገባ የመጀመሪያ የትምህርት ምርጫህ ምን ነበር?

ጋዜጠኛ ጥበቡ:- አራቱን ባዶ አድርጌ አንድ ምርጫ ብቻ ነው የመርጥኩት። ቋንቋና ጋዜጠኝነትን እወድ ስለነበር እርሱን ነው የመረጥኩት፡፡ እንደውም ምርጫህ ይሰረዛል እያሉ አስፈራርተውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ቤተሰቦቼ ህክምና የማጠና መስሏቸው ነበር፤ ውጤቴም ለዚያ የሚያበቃ ነበር፡፡

እኔ በጣም እድለኛ ነኝ። ለምን አልኩህ መሰለህ በልጅነቴ ጋሽ ሰለሞን ገብረሥላሴ ዛሬም በህይወት አለ በልጅነቴ ክረምት ክረምት ወስዶኝ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ‘‘ከልጆች ዓለም” የሚለውን የልጆች ፕሮግራምን ከአዘጋጆቹ ውስጥ አንዱ ሆኜ እንዳቀርብ ያደርገኝ ነበር፡፡ ከእነ ብርሃኑ ገብረማርያም፣ እመቤት ወልደገብርኤል፣ አሁን በውጭ ሀገር ከምትኖረው ቅድስት በላይና ሌሎችም ጋር እሰራ ነበር፡፡ በዚህም ወቅት ለልጆች ፕሮግራም ሃሙስ ሃሙስ እቀረፅ ነበርና ለምፅፋቸው ነገሮች በደንብ ማንበብ ጀመርኩ። ድምጼ አየጎረና ሲመጣ አባት በመሆን መስራት ጀመርኩኝ፤ ከዚያም ዩኒቨርሲቲ ስገባ እዚያው ኢትዮጵያ ሬዲዮ ከወጣቶች ለወጣቶች የሚል ፕሮግራም ላይ ጽሁፍ በመጻፍ መሳተፍ ጀመርኩኝ፤ በአጠቃላይ ልጅነቴን ሬዲዮ ውስጥ ነው ያሳለፍኩት ማለት ይቻላል፡፡

ንጋት:- በኢትዮጵያ ሬዲዮ ምን ያህል ጊዜ አገለገልክ?

ጋዜጠኛ ጥበቡ:- ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅኩ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ፋይል መጀመሪያ የገባሁበት ነበር፡፡ ከእነ እሸቱ ገለቱና ብርቱካን ሃረገወይን ጋር አለቆቼ ሆነው ጥቂት ወራት ነው የሰራሁት። የመመረቂያ ጽሁፌንም የሰራሁት ዜና  ላይ ነው፤ የዜና አቀራረብ በኢትዮጵያ የሚል ነበር። እነርሱም ተሻምተው ነበር ሊወስዱኝ የነበረው፡፡

ወዲያው ደግሞ አዲስ ብሮድካስቲንግ ካምፓኒ የሚባልን የአሁኑ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ጓደኞቻቸው ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጣ ለመክፈት አስበው ያቋቋሙት ድርጅት ነበራቸው። እርሳቸው ከውጭ እንደመጡ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምሩ ተዋውቀውኝ ነበርና እኔ ገና ከዩኒቨርሲቲ ከመመረቄ ወሰዱኝና ገና ስራ እንደ ጀመርኩ የውጭ እድል በእርሳቸው አመቻችነት አገኘን፡፡

የኖርዌይ መንግስት ”ኖራድ‘’ የሚባል አሁን ድረስ ያለ የእርዳታ ድርጅት ታዳጊ ሃገሮች ላይ የሚዲያ ዴሞክራሲን ለማስፋፋት ጥረት ስለሚያደርግ የእኛን በምህጻሩ ”ABC‘‘ የሚባል ድርጅት ይረዳ ስለነበር የድርጅቱ መስራቾች ተብለን የሙያ ትምህርት መስጠት ስለነበረበት ኬንያ ናይሮቢ ወስዶን ለስድስት ወር አካባቢ ስልጠናና ትምህርት ወስደን በፖስት ግራጁዌት ዲፕሎማ በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ወሰድን፡፡ ይህም በአንድ አመት ሁለት ድግሪ አገኘን ማለት ነው፡፡

ንጋት:- እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ያሰቡት የግል ሬዲዮ ጣቢያ የመክፈት ዕቅድ ሳይሳካ ሲቀር ጋዜጣ ጀምራችሁ ነበር፤ ስለ እርሱ አጫውተን እስቲ!

ጋዜጠኛ ጥበቡ:- ሬዲዮ ሲዘገይብን ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ዜና የሚባል ጋዜጣ ጀመርን፤ በጣም ታዋቂ ጋዜጣ ነበር። በወቅቱ በየሳምንቱ ረቡዕ ነበር የሚታተመው፤ ወደ ሃምሳ ሺህ ኮፒ ገና ሲጀመር ይታተም ነበር። ከዚያም ውስጥ አስር ሺህ ኮፒ ሰሜን አሜሪካ፣ ወደ ሶስት ሺህ ኮፒ አውሮፓ፣ እንዲሁም ሁለት ሺህ ኮፒ አፍሪካ ይላክ ነበር፤ የቀረው ሃገር ውስጥ ይሰራጭ ነበር፡፡ ጋዜጣው ከቀኑ ስድስትና ሰባት ሰዓት ያልቅ ነበር፡፡

ከኬንያውና ኖርዌዩው በኋላ ለንደን የሚገኘው ሮይተርስ ፋውንዴሽን ለአፍሪካ ጋዜጠኞች ነጻ የትምህርት ዕድል ይሰጥ ነበር። አውሮፓ ሄደው ሳይሆን እርስ በርስ አፍሪካ ውስጥ እንዲማሩ ነበር እድሉን ያመቻቸው።

ያንን ዕድል እኔና አንዲት አዳነች የምትባል ልጅ አግኝተን ከአስራ አንድ የአፍሪካ ሀገራት ከተወጣጡ ተማሪዎች ጋር በደቡብ አፍሪካ ሮድስ ዩኒቨርሲቲ የሬዲዮ ጋዜጠኝነትና ሚዲያ ማኔጅመንትን በተመለከተ ለሰባት ወራት ተማርን፡፡ ዓላማውም ኢትዮጵያ ውስጥ ገና የግል ሚዲያዎች ሊመጡ ነው እየተባለ ነገር ግን የተማረ የሰው ሃይል የለም ስለሚባል ያንን ክፍተት ለመሙላት ታስቦ ነው፡፡

የሚገርመው ነገር ታዲያ የአፍሪካ መዲና ለአፍሪካ ነጻነት የታገለች… ወዘተ በምትባለው ኢትዮጵያ ሬዲዮ የላቸውም ሲባል ብዙዎች ይገረሙ ነበር። በአንጻሩ እኛ እናፍር ነበር፡፡ የነበረውም አንድ ለእናቱ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው፤ ኤፍ ኤም አዲስም ቢሆን የመንግስት ነው፡፡ እናም ከሌሎች ሃገራት የመጡት ሲፎግሩን ታዲያ ሬዲዮ ሳይኖራችሁ ነው እንዴ ስለ ሬዲዮ የምትማሩት ይሉን ነበር። ሌላው ከሚገርመው ነገር ደግሞ እኛ ሬዲዮም በሌለበት ጭራሽ ዲጅታል ኤዲቲንግ  ነው እየተማርን የነበረው፡፡

እርሱም ለእኛ ከባድ ነበር፤ ምክንያቱም በዚያን ወቅት የአይቲም ጉዳይ በጣም ደካማ ነበር፡፡ ጽንሰ ሃሳቡ አያስቸግረንም ነበር። በተግባር ሲደገፍ ግን ትምህርቱ ጊዜ ይወስድብን ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ብዙ ትምህርት ያገኘሁበት ነው ብዬ የማስበው ሮድስ ዩኒቨርሲቲ የተማርኩበትን ጊዜ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሮድስ ዩኒቨርሲቲ ድሮ ነጮች ብቻ የሚማሩበት ነበር፡፡ እናም ደቡብ አፍሪካ ገና ጥቁሮች ትምህርት ቤት ገብተውና ዩኒቨርሲቲ ጨርሰው ወደ ስራ ዓለም እየገቡ ያለበት የሽግግር ወቅት ነበር እኛ የሄድንበት ጊዜ፡፡

ንጋት:- በስነጽሁፍም ትልቅ ስም ነው ያለህና እንዴት ነው ያዳበርከው?

ጋዜጠኛ ጥበቡ:- ገና በልጅነቴ ለስነጽሁፍ ልዩ ፍላጎት ስለነበረኝ እፅፍ እና በዙሪያዬ ላሉ አነብላቸው ነበር። የእነርሱም ግብረ መልስ አበረታች እና በዚሁ እንድገፋበት የሚያደርግ በመሆኑ ይህ የሞራል ስንቅ ሆኖልኛል፡፡

ስነጽሁፉ ላይ ያለኝ የበሰለ እውቀት የመጣው እጅግ በተመስጦ በማድመጤ ነው። ሬዲዮ ማድመጥ ከመፃፍም በላይ የምወደው ነው፡፡ ሱስ የሆነብኝ ሬዲዮ ማድመጥን ንጉሴ አክሊሉ፣ ታደሰ ሙሉነህ፣ ታምራት አሰፋን የመሳሰሉትን አንጋፋ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የጳውሎስ ኞኞ አስደናቂ ፅሁፎችን እየሰማሁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ያሳለፍኩ ሲሆን ይህ ደግሞ ከፍ እንዲል በእነርሱ ደረጃ እንዲመጣ ትልቁን አስተዋፅኦ አድርጎልኛል።

በጊዜውም ደግሞ በተለያዩ ጋዜጦች በተለይ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ተከታታይ ፅሁፎቹ ይታተሙልኝ ነበር፡፡

ንጋት:- “ኮፕሬቲቭ ወተር” (Cooperative Water) በሚል ርዕስ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚወጣ መጽሄት እንደነበራችሁ መረጃው አለንና ስለእርሱ ንገረን!

ጋዜጠኛ ጥበቡ:- የአሥርቱን ተፋሰስ ሀገራት ጉዳይ እና የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ብዙ ምሁራኖች የሚፅፉበት በየስድስት ወሩ የሚታተም መፅሔት አቋቁመን ነበር። ይሁን እንጂ የተለያዩ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች በሚያነሱት ጥያቄና አትፅፉም ሲሉ በሚፈጥሩት ወከባ ሳቢያ ብዙ ርቆ ሳይጓዝ ለመቋረጥ ተገዷል።

መጽሄቱ በአንድ ጆርናል ህትመት ብቻ የቀረ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አሁን ላይ ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያልተገባ ነገር ሲያወሩ ሊከራከሩ የሄዱት ኢትዮጵያዊያን በዚያ መጽሄት ላይ የጻፉ ስለነበሩ ይዘውት የሄዱት የዚያኔ የጻፉትን ለኢትዮጵያ ክርክር ያገለገለ ሀሳብ ነበር። መጽሄቱ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ለሀገር ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ስለዚህ አሁንም መቀጠል ያለበት ይመስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ ለስራው ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ኢንተርቪው ማድረግ ስለነበረብን ይህ አጋጣሚ አፍሪካን እንደራሴ ሀገር እንዳውቃት እድል የፈጠረልኝ ስራ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የሚባል ዘርፍ አለ። እዚያ ውስጥም አባል ነኝ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ማህበርን ለሶስት አመት ያህል በፕሬዝዳንትነት አገልግያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን በዋና ጸሀፊነት በማገልገል ላይ እገኛለሁ። በጣም ብዙ ቦታዎች ላይ የቦርድ አባል ነኝ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ጤና ስለሰጠኝ ደስ ብሎኝ ነው የምሰራው፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያ በቆየሁባቸው ጊዜያት በርካታ ትልልቅ ሰዎችን አግኝቻቸው ቃለ መጠይቅ ላደርግላቸው ችያለሁ። ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ፣ አንጋፋው ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ፣ አንጋፋው የኢትዮጵያ ሙዚቀኛ ጥላሁን ገሰሰ፣ አስናቀች ወርቁ፣ እና የትዝታው ንጉሥ ጋሽ ማህሙድ አህመድ እና ሌሎችም፡፡

ንጋት፡- ሁለተኛ ድግሪህን በምን ዘርፍ ነው የሰራኸው?

ጋዜጣኛ ጥበቡ፡- ሁለተኛ ድግሪዬን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶኪዩመንተሪ ሊንጉዊስቲክ ኤንድ ከልቸር (Documentary linguistic and culture) በሚባል የትምህርት ዘርፍ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ተዘግቷል፡፡ በዩኔስኮ ድጋፍ የመጣ ትምህርት ሲሆን አደጋ ውስጥ ለገቡ ቋንቋዎች እንዳይጠፉና ባህልና ታሪክን እንዴት ዶክምንት እናድርጋቸው በሚል የተጀመረ ትምህርት ነበር፤ አንድ ግራዚያኖ ሳቫ የሚባል ጣሊያናዊ ፕሮፌሰር ነበር ፕሮጀክቱን ያመጣው፡፡ እኔም ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ነበርኩ፡፡ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በመንግስት የመጡ የባህልና ቱሪዝም ሃላፊዎች ሲሆኑ እኔ በግሌ ከፍዬ ነው የተማርኩት፡፡ ያ ትምህርት ታዲያ ለዶክመንተሪ ስራ በጣም ነው የጠቀመኝ፡፡

ለምሳሌ ደቡብ ላይ ከፕሮፌሰር ግራዚያኖ ጋር ወደ ሐመር ሄደን የጸማይኮችን ቋንቋቸው አሁን ያለ አይመስለኝም “ኦንጎታ” የሚባል ብሄረሰብ ዘጠኝ ብቻ ነበር፤ የዚያን ጊዜ የቀሩት እና ፕሮፌሰር ግራዚያኖ እነዚያን ዘጠኙን ሰዎች ኢንተርቪው አድርጎ ዘፈናቸውን ሲዘፍኑ ቋንቋቸውን ዶክመንት አድርጎ ወደ ሀገሩ ይዞ ሄዷል፡፡ ከእነዚያ ሰዎች መካከል አንዱ ብቻ ነበር ወጣት፡፡ ስምንቱ አሁን ላይ በህይወት መኖራቸውን እጠራጠራለሁ፡፡

ያ የተሰነደው ለምን መሰለህ የሚያገለግለው ቋንቋው ቢጠፋም መልሶ ማምጣት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የእብራይስጥ ቋንቋ እስራኤሎች ሲበተኑ በዓለም ላይ ጠፍቶ ነበር፤ ዶክመንት በመደረጉ ግን እንደገና እብራይስጥን አምጥተውት ዛሬ ቋንቋው በዓለም ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ፣ የጥናትና ምርምር ቋንቋ መሆን ችሏል፤ እንደገና ወልደውታል፡፡ ልክ እንደዚያው ሁሉ ”Documentary linguistic and culture” የሚባለው ትምህርት ቋንቋዎችንና ታሪኮችን እንደገና ዶክመንት አድርጎ መመለስ ያስችላል፡፡

እኔ ለምሳሌ ሁለተኛ ድግሪዬን የሰራሁት በሀረሪ ብሄረሰብ ላይ ነው፤ ምክንያቱም እነርሱም በቁጥራቸው ማነስ ምክንያት ታሪክና ቋንቋቸው ለአደጋ እንዳይጋለጥ መሰነድ ያስፈልገዋልና ነው፡፡

ንጋት፡- የቲያትር ሰው እንደ ሆንክም ሰምተናልና በቲያትሩ ዘርፍ እንዴት ነህ?

ጋዜጠኛ ጥበቡ፡- ዋና ዋና መድረኮች ላይ ባልወጣም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መድረኮች ላይ ቲያትሮችን ሰርቻለሁ፡፡ እንደውም የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ቲያትር ላይ ከባዱን የሃምሌት ገጸባህሪ ወስጄ ተውኛለሁ፡፡ እንደገና ጌታቸው ታረቀኝ የጻፈው ካሊጉላ ተውኔት ላይ ኦክታአበስ የሚባል ገጸባሪ እና ሌሎችንም ተጫውቻለሁ። ግን ስክሪፕት ማጥናት ነው የሚከብደኝ፡፡ ምክንያቱም ለጋዜጠኝነቱ ስራ ቅድሚያ ስለምሰጥና ለትወናው ሙሉ ጊዜዬን ስለማልሰጥ ስክሪፕቱን መያዝ ያስቸግረኛል። ከያዝኩት ግን ትወናው ላይ በጣም ጎበዝ ነኝ፡፡ ተፈጥሮዬን ሳየው ግን ተሰጥኦዬ ዳይሬክቲንግ ይመስልኛል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ትንግርትና ምስጢራት የሚል የሰራነው ብዙ ጊዜን የፈጀ፣ ብዙ ገንዘብ የወጣበት በርካታ ጥናቶች የተካሄዱበትና ባለሞያዎች የተሳተፉበት የታሪካዊው ቅዱስ ላሊበላ ዶክመንተሪን በመስራት በ1999 ዓ.ም ወይም እ.ኤ.አ በ2007 በለንደን የሚገኘው የብሪቲሽ ሙዚየም አፍሪካ ላይ የተሰሩ ባህል፣ ታሪክ በእምነት ላይ የተመሰረቱ ሥራዎችን ሲመርጥ የላሊበላው ዶክመንተሪ ፊልም አሸናፊና ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። ይህ ዶክመንተሪ ከፍተኛ የሆነ እውቅናን አግኝቶ በብሪቲሽ ለንደን ሙዚየም ውስጥ ለመታየት የቻለ ሲሆን እኔንም ለዓለም ህዝብ ያስተዋወቀ ነበር።

ከዚያም የጎንደርንና የአክሱምን ታሪክ ሰርተናል። የሃረርን በተለይም “ዳርመሸህ” ማለትም ሀረር ውስጥ ያሉ ጅቦችን በተመለከተ ታሪክንና ባህልን የቀረሰና በጣም የተወደደ ዶክመንተሪም ሰርተናል፡፡

ንጋት፡- የጥበቡ በለጠ ስም ሲጠቀስ የታሪክ ተመራማሪ የሚል ቅጽል ከፊት ይመጣል፤ ለመሆኑ የታሪክ ተማሪም ነበርክ?

ጋዜጠኛ ጥበቡ፡- በጣም ይገርምሀል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው ዓመት ከወሰድኩት ውጭ እኔ ታሪክ አልተማርኩም። ብዙዎቹ የዩኒቨርሲቲ መምህራኖቼ ስለ ታሪክ ሳወራ ሲሰሙ አንተ ታሪክ ተምረህ ቢሆን እያሉ ይገረማሉ፤ ብማር ምናልባት ብዙ ላልጽፍ እችላለሁ፡፡ ሆኖም ግን ከልጅነቴ ጀምሮ የታሪክ አፍቃሪ ነኝ፡፡ ሰዎች የታሪክ ተመራማሪ ሲሉኝ አፍራለሁ፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ግን እንደ አንተ ማን ተመራመረ ይሉኛል፡፡ በዚህ ደግሞ ደስ ይለኛል፡፡ ሞራልም ይሆነኛልና በዚያ ምክንያት ነው ወደ ታሪክ ያዘነበልኩት፡፡

ንጋት፡- ጨዋታችንን እያገባደድን ነውና የመጨረሻ ጥያቄ፡- አሁን ላይ ያለውን የጋዜጠኝነት ሙያ እንዴት ትገልጸዋለህ?

ጋዜጠኛ ጥበቡ፡- የጋዜጠኝነት ሙያ ዘርፈ ብዙ ነው አደገ የምትልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በእኛ ጊዜ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶች አልነበሩም፡፡ በነገራችን ላይ ኖርዌዮቹ እኛን ለማሰልጠን መጥተው ከዚያም እኛን ጨምሮ ሌሎቹንም ወደ ኖርዌይ ሲወስዱን የተመለከቱት የአሁኑ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለኖርዌያኖቹ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥያቄ አቅርበው ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው፡፡ ይህንን አስምርበት ፕሮፌሰሩ ለጋዜጠኝነት ትምህርት መከፈት ባለውለታ ናቸው፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በሃዋሳና በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍሎች መከፈታቸው ትልቅ እድገትና እምርታ ነው። በተጨማሪም ባለፉት ስድስትና ሰባት አመታት ትልልቅ ለውጦች ያሉበት የመገናኛ ብዙሀን ህግና የሚዲያ ፖሊሲ ወጥቷል፡፡ እነዚህ ነገሮች በሀገሪቱ ውስጥ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ የሚዲያዎች መስፋፋት የሚያበረታታ ቢሆንም በሙያው ጥራትና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ በመፍጠር በኩል የማደጉ ነገር ሲታይ ደግሞ ገና ነው፡፡

ንጋት፡- ስለነበረን ጊዜ በዝግጅት ክፍላችን ስም እጅግ አመሰግናለሁ፡፡

ጋዜጠኛ ጥበቡ፡- እኔም በድጋሚ በጣም አመሰግናለሁ፡፡