የልጆች የክረምት ውሎ
ውድ አንባቢያን እንደምን ቆያችሁ? ለመላው ወላጆች እንኳን ለወላጆች ቀን በሰላም አደረሳችሁ/አደረሰን! የልጆቻችሁ ውጤት እንዴት ነበር? እነሆ የትምህርት ዓመቱ ተጠናቆ ትምህርት ቤቶች የወላጆች በዓል እያከበሩ ያሉበት ሳምንት ላይ ደርሰናል። በዚህ በወላጆች ቀን ተማሪዎች የዓመት የጥረት ውጤታቸውን የሚያዩበት ቀን ነው፡፡
ጥሩ የሠራ ተማሪ የሚሸለምበት፣ የተዘናጋ ተማሪ ደግሞ የሚፀፀትበት በመሆኑ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችም በልጆቻቸው ውጤት የሚደሰቱበት አልያም ደግሞ የሚፀፀቱበት ነው፡፡
መዘናጋቱ የሚጀምረው ገና ትምህርት ቤት ከመዘጋቱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች በስነ-ምግባር ዓመቱን ሙሉ አንፀው ሲያስረክቡን በወራት ውስጥ አደራቸውን መብላት የለብንም፡፡
የክረምት ውሏቸውን መርጠን በስነ-ምግባር እና በእውቀት ገንብተን ለቀጣይ ዓመት ልጆችን ዝግጁ ማድረግ የወላጅ ግዴታ ነው፡፡
የእረፍት ጊዜያቸውን እንዴት ያሳልፉ የሚለው ትኩረት መሰጠት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የክረምት ወቅት ለተማሪዎች ረጅም የእረፍት ጊዜ በመሆኑ በምን አግባብ ያሳልፉት የሚለው የአብዛኛው ወላጅ የቤት ሥራ ነው፡፡
ልጆች ዓመቱን ሙሉ ተጨናንቀው ስለሚያሳልፉ ባላቸው የዕረፍት ጊዜ ዘና ማለት ይፈልጋሉ፡፡ ታድያ የልጆችን የልብ ማሻት እውን ለማድረግ በምን አግባብ ማሳለፍ እንዳለባቸው ሁሉም ወላጅ በጥንቃቄ ማስተዋል አለበት፡፡
በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤት አካባቢ ያሉ ልጆች የክረምት ውሏቸው አሳሳቢ ነው የሚሆነው፡፡ ምንም አይነት የመጫወቻ ሥፍራ የላቸውም፡፡
በየደጃፉ ሲጫወቱ ይታያሉ ግን ከየቤቱ የሚደፉ ቆሻሻዎች የጤና ችግር ሲያደርሱባቸው ይስተዋላል፡፡ ሀዋሳ የምትታወቅበት አንዱ በከተማ ውበቷ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በየሰፈሩ ያለው ጉድ ውስጡን ለቄስ ያስብላል፡፡ ማህበረሰቡ ስለ አካባቢ ፅዳት ገና አልገባውም፡፡ የገዛ ልጆቻቸው አያሳዝኗቸውም፤ እንደፈለጉ ቆሻሻ አውጥተው ይደፋሉ፡፡
አንዳንዴ በልጆችም አይፈረድም። ምቹ ሁኔታ አልፈጠርንላቸውም፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ የልጆች መጫወቻ ሥፍራ መታሰብ ነበረበት፡፡ በእነዚህ መሰል ምክንያቶች ልጆች ከእኩዮቻቸው ጋር ከመጫወት ይልቅ ቤት ውስጥ ቴሌቪዥንና ስልክ በመነካካት ለማሳለፍ ይገደዳሉ፡፡
የሚያዩትን ቻናል (ፕሮግራም) እንኳን አይመርጡም፡፡ ከጥዋት እስከ ማታ እዚያው ላይ እንደደነዘዙ ይቀራሉ፡፡ ትምህርት ቤት ሲከፈት ሁሉ ነገር አዲስ ይሆንባቸዋል፡፡ ምንም አይነት ነገር ማንበብም ሆነ ማጥናት አይፈልጉም፡፡ ታድያ ትምህርታቸው ላይ ተፅዕኖ ሲፈጥር ይታያል፡፡
መጫወቻ ቦታ ያላቸው ልጆችም ቢሆኑ በየአካባቢው የምንመለከተው ምንም አይነት ፕሮግራም የላቸውም፡፡ ማለዳ ኳስ ሲጫወቱ ያየናቸው ልጆች ምሽት ብንሄድ እዚያው ሲራገጡ እናያቸዋለን፡፡ የምግብ ሰዓታቸውን እንኳን አይጠብቁም፡፡
አሁን አሁን ላይ ደግሞ ቡድን ፈጥረው ውድ የሆነ ስልክ ይዘው እንደ ስልክ እንጨት በየመንገዱ ጥግ መገተር ፋሽን እየሆነ መጥቷል፡፡
ወላጅ በየመንገዱ እነዚህን ተግባራት ማየታቸው አይቀርም፡፡ ነግ በእኔ ብለው ለምን ለልጆቻቸው ስልክ እንደሚሰጡ አይገባኝም። ለነገሩ ዘመናችን ሁሉ ነገሩ በስልክ ሆኗል ጨዋታው፡፡ ያው ሙሉ በሙሉ መከልከል ባይቻልም መከታተል ግን ይቻላል ባይ ነኝ፡፡
ወላጆች የስልክ አጠቃቀማቸውን ክትትል ማድረግ አለባቸው፡፡ የጋራ መኖሪያ አካባቢ ያሉ ልጆችን መቆጣጠር አዳጋች ነው፡፡ እኛ ብንከለክላቸው ከጓደኞቻቸው ጋር ማየታቸው አይቀሬ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ልጆችን ማሳደግ ቢከበድም አደራ ናቸውና ሳንሰለች እንደምንም ተቸግረን ከዓይናችን ሳይርቁ ተንከባክበን ለፍሬ ማብቃት አለብን፡፡
ልጆች የፈጣሪ ፀጋ ናቸው፡፡ ልጆችን አስመልክቶ የፈጣሪ ቃል ብዙ ነገሮችን አስቀምጦልናል፡፡ የፈጣሪን ቃል ለመጠበቅ የተሰጠንን አደራ ተቀብለን ሀላፊነታችንን መወጣት አለብን፡፡
ልጆቻችንን ከታች ጀምሮ ትኩረት ሰጥተን ካልያዝናቸው መጥፋታቸው የግድ ነው፡፡ በተገቢው መንገድ የፈጣሪን አደራ ካልተወጣን ችግሩ መልሶ ለኛው ነው። ስለዚህ ለልጆችችን ትኩረት ሰጥተን ፕሮግራም አውጥተን በተለይ የክረምት የዕረፍት ጊዜያቸውን ከእኛ ጋር የሚቆዩት ሰፊ ጊዜ ስለሆነ መከታተል አለብን።
ልጆች የዕረፍት ጊዜያቸውን ከለመዱት የትምህርት ቤት አካባቢ ውጭ ሆነው ስለሚያሳልፉ በመሰላቸት ድብርት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ መሰላቸት እንዳይመጣ ያላቸውን የዕረፍት ጊዜ በሰዓት መከፋፈል ያስፈልጋል፡፡ በፕሮግራማቸው መሠረት ጊዜያቸውን በአግባቡ ከተጠቀሙ የክረምት ጊዜያቸው ጣፋጭ ሆኖ ነው የሚያልፈው፡፡
እኛንም ሲወጡ ሲገቡ ውሃ ቀጠነ እያሉ አይጨቀጭቁንም፡፡ አንዳንዴ ጭቅጭቃቸው ሲሰለቸን ስልክ ወርውረን አፋቸውን ልናዘጋ እንችላለን፡፡ ለጊዜው እፎይታ ብናገኝም ዞሮ ዞሮ ፀፀቱ ለእኛው ነው፡፡
ውድ ወላጆች የትውልድ ተወቃሽ እንዳንሆን ፈጣሪን እንዲፈሩ እንደየእምነታችን የተወሰነ ሰዓት ወስደው የፈጣሪን ቃል እንዲማሩ ማድረግ፣ እንደ ዕድሜያቸው የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ እንዲሁ እንደ እጅ ሥራ፣ የሸክላ ሥራ፣ የእንጨት ሥራ፣ የወረቀት ሥራ እና የሥዕል ሥራ የመሳሰሉትን ወላጆች አብረው እየሠሩ ማለማመድ ይጠበቅባችኋል፡፡
በተጨማሪም ጤናቸውን እንዲጠብቁ ስፖርት እንዲያዘወተሩ ማድረግ ለምሳሌ እንደ ቴኳንዶ፣ ዋና፣ እግር ኳስ እየተጫወቱ ቢያሳልፉ አዕምሯቸውን ያጎለብታሉ፡፡
አካባቢያቸውንም ሊሆን ይችላል ወጣ ብለውም ሀገራቸውን እንዲያውቁ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ጥሩ ነው፡፡ በተላይ ሀዋሳ ላይ ያሉ ልጆች ብዙ የሚጎበኙ አማራጮች ስላላቸው ብዙም ወጪ ሳያወጡ መጎብኘት ይችላሉ፡፡
የማንባብ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ የተለያዩ መጽሐፍቶችን መግዛት ከወላጅ የሚጠበቅ ነው። እንደ ተረት መጽሐፍት እና የታሪክ መጽሐፍት እንዲያነቡ ማድረግ። ያነበቡትን መልሰው እንዲነገሩን መጠየቅ እና አቅም ከፈቀደ የቀጣይ ትምህርታቸውን ቀድመው እንዲዘጋጁ የክረምት ትምህርት ማስገባት፡፡
ቅድመ አንደኛ ደረጃ ላሉ ተማሪዎች ደግሞ ቤት ውስጥ ፊደላትን እና ቁጥሮችን እንዲለዩ ማድረግ በትምህርት ቤት መምህራንን ያግዛሉ፡፡ ክረምት ላይ ከወላጅ ጋር የሠራ ተማሪ መስከረም ላይ ውጤታቸው ይቀራል፡፡
ከቤት ሳይወጡ የተለያዩ ጨዋታዎችን እንዲጫወቱ ማድረግ እንደ አኩኩሉ፣ እቃቃ እና የብይ ጨዋታ የመሳሰሉትን አብረናቸው መጫወት፡፡
ቋንቋቸውን እንዲያዳብሩ የተመረጡ ፊልሞችን ማሳየት፡፡ ያዩትን መልሰው እንዲነግሩን ማድረግ፡፡
እንደ ሚታወቀው የጋራ መኖሪ ቤቶች የአትክልት ሥፍራ የላቸውም፡፡ በዕቃ ተክለው የራሳቸውን የአትክልት ቦታዎችን እንዲንከባከቡ ማድረግ፡፡ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን እንዲያጠናክሩ ዘመድ ጎረቤት እንዲጠይቁ ማለማመድ፡፡
ቤት ውስጥ ምግብ ማብሰል እንዲለማመዱ ማድረግ፡፡ እርስ በርሳቸው የምግብ ውድድር እንዲያደርጉ ማበረታታት እና የራሳቸውን ልብስ እንዲያጥቡ ማድረግ ሥራ እንዲለምዱ ያግዛል። አጠቃላይ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲያግዙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ወላጅ ትልቅ ሃላፊነት የሚሸከመው ክረምት ላይ ነው፡፡ ወላጅ በትክክል ክትትል አድርጎ የላከው ተማሪ ውጤታማ ነው የሚሆነው፡፡
እንግዲህ እነዚህን የክረምት ተግባራት ተግባራዊ ለማድረግ የወላጆችን ፅናት ይጠይቃል። ወላጆች ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ የልጆች የክረምት የዕረፍት ጊዜያቸው ላይ መስዋዕትነት መክፈል አለባቸው፡፡ በተለይ ከፍ ያሉ ልጆች ያሏችሁ ወላጆች ልጆቻችሁን መውጫና መግቢያቸውን በአንክሮ መከታተል ያስፈልጋል፡፡
“የእኔ ልጅ ጨዋ ነው፤ እንዲህ አያደርግም፤ የእገሌ ልጅ ነው እንዲህ የሚያደርገው” ብሎ ድፍን ያለ ብይን ከመስጠት እንቆጠባለን፡፡ የራሳችንን ልጅ አንፀን ካሳደግን ለጎረቤቶቻችን አርዓያ እንሆናለን፡፡
እስቲ ለመጪው ዓመት በዕቅዶቻችን መሠረት ተግብረን ለሌሎች ምሳሌ እንሁን መልዕክታችን ነው!!
More Stories
“በእጅ ጋሪ ያመላልሱኝ ነበር” – ተወዳ መንጌ
የስም ነገር
“እግር ኳስ ቢያሳምመኝም ቂም አልያዝኩበትም”