በጎፋ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1 ሺህ 830 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1 ሺህ 830 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የጎፋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በዞኑ ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና መሸፈኑ ተገልጿል።
በጎፋ ዞን የቡና ጥራት ቁጥጥር አስተባባሪ ግብረ ኃይል የ2017 አፈጻጸምና 2018 ዕቅድ ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ በተካሄደበት ወቅት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ እንደገለጹት፥ ዞኑን በሐገር አቀፍ ደረጃ በቡና ምርት ተወዳዳሪ ለማድረግ ቡናን በሰፊው ማምረት፣ ጥራትን ማስጠበቅና ሕገወጥነትን በጋራ መከላከል እንደሚገባ አብራርተዋል።
ጥራት የሌለው ምርትና ሕገወጥ ግብይት አምራቹ እና ሸማቹ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም የሚያሳጣ ከመሆኑ ባሻገር ዞኑ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ የሚያሳጣ በመሆኑ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ቡና ለአካባቢው ማህበረሰብ ከኢኮኖሚ አልፎ የማህበራዊ መስተጋብር መገለጫ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፥ ይህንን ልዩ እሴት በአግባቡ ለመጠቀም በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ በዞኑ ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቡና የተሸፈነ መሆኑን አንስተው የቡና ምርታማነትን ለማሳደግና ጥራቱን ለመጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የቡና ምርታማነትን በማሣደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለመጨመር ያረጁ የቡና ዛፎችን ከመጎንደል ባለፈ አዳዲስ የቡና ችግኞችን ተከላ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዞኑ ቡና በከፍተኛ ሁኔታ የሚመረት በመሆኑ ምርቱን ወደላቀ ኢኮኖሚያዊ እሴት መቀየር በሚቻልበት ሁኔታ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
የጎፋ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑርአድስ አደም በዞኑ በ 2017 ዓ.ም 1 ሺህ 590 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 1 ሺህ 830 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መላኩን ገልፀዋል።
በ2018 የበጀት ዓመት ከ2 ሺ 100 ቶን በላይ ለማዕከላዊ ገበያ ለመላክ ስለመታቀዱ የገለጹት ኃላፊው፥ በህገ-ወጥ የቡና ዝውውር ላይ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በተሠራው ሥራ 178 ኩንታል ቡና በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተይዞ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ለዞኑ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
አርሶአደሩ የቡና ምርታማነትን በማሳደግ ውጤታማ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
በቡና ንግድ ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል አቶ ተመስገን ካሳዬ እና አቶ እንዳለ እንግዳ ጥራት ያለውን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የተሻለ ጥቅም ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በያዝነው የበጀት ዓመትም በዘርፉ ውጤታማ ተግባር ለመፈጸም ስለመዘጋጀታቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በተገቢ መደገፍና ማበረታታት ለሃገር ኢክኖሚ እድገት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተገለጸ
በመኸር እርሻ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ይጠበቃል – የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ
በጌዴኦ ዞን የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ተገለጸ