በመኸር እርሻ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ይጠበቃል – የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
”ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ቃል የ2017/18 ዓ.ም የመኸር እርሻ ልማት ሥራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በዞኑ ቡሌ ወረዳ ኮቾሬ ቀበሌ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በመርሀ ግብሩ የቡሌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ሽፈራው በወረዳው በ2017/18 የመኸር እርሻ ልማት ከ4 ሺህ 900 ሄክታር መሬት በአዝርእት ሰብልና ሆልቲካልቸር ለማልማት መታቀዱን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ ከ500 ሄክታር በላይ መሬት በክላስተር የሚለማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ አበበ ገለጻ ከመኸር ልማት ሥራ ከ900 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ለዚህም የዘርፉ ባለሙያዎች አርሶ አደሩን በቅርበት ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉለት አስታውቀዋል፡፡
የቡሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በራሶ በበኩላቸው ወረዳዋ በስፋት በገብስ፣ ባቄላ፣ ድንችና በሌሎችም የሰብል ምርቶቿ የምትታወቅና በተለይም ወደተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በሚላከው የቅጠል ሽንኩርት ምርት ታዋቂ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በአገር ደረጃ የተጀመረው ጥረት አካል በመሆኑ የአከባቢው አርሶአደሮች በግብርና ልማት ሥራዎች የነቃ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ በራቆ አሳስበዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ታጠቅ ዶሪ፥ በዞኑ በበልግ የልማት ወቅት ከነበረው ጠንካራ አፈጻጸም በመነሳትና የነበሩ ጉድለቶችን በማረም በመኸር በቂ የእርሻ ዝግጅት በማካሄድ በዛሬው ዕለት ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል፡፡
በዞኑ ቡሌን ጨምሮ በራጴና ጮርሶ ወረዳዎች በአሲድ የተጠቁ መሬቶችን ለማከም ከ18 ሺህ በላይ ኩንታል ኖራ መሰራጨቱንና ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለሚደረገው ጉዞ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንና በአጠቃላይ ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር እርሻ ለማልማት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡
በአንዳንድ የዞኑ አከባቢዎች የሚስተዋሉ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ማሽነሪዎችን ግዢ በመፈፀም አዳዲስ መንገዶችን የመክፈትና የነበሩትን የመጠገን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፥ ይህ አርሶ አደሩ ያመረተውን ወደ ገበያ እንዲያወጣ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
ካነጋገርናቸው የቡሌ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ሉቃስ ዱቤ፣ አበራ ገደቾ እና ሌሎችም ለመኸር እርሻ መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ ማዘጋጀታቸውንና በግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ መሠረት በመስመር በመዝራት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በተገቢ መደገፍና ማበረታታት ለሃገር ኢክኖሚ እድገት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተገለጸ
በጎፋ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1 ሺህ 830 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡ ተገለጸ
በጌዴኦ ዞን የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ተገለጸ