በጌዴኦ ዞን የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ተገለጸ

በጌዴኦ ዞን የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጌዴኦ ዞንን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።‎

‎የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ደርቤ ጂኖ በዞኑ ያለው መልከአ ምድርና በውስጡ ያለ የቱሪስት መዳረሻዎችን የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅመው እያስተዋወቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።‎

‎በማህበራዊ ገጾች፣ በተለያዩ ሚዲያዎችና በዌብ ሳይቶች የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊው፥ የጌዴኦ መልከአ ምድር አያያዝ በዩኔስኮ የተመዘገበ መሆኑ፣ የቡና ቱሪዝም እና የደራሮ በዓልም ለዘርፉ ዕድገት አዎንታዊ አስተዋህጾ አድርገዋል ብለዋል።‎

‎ከጌዴኦ መልከአ ምድር አያያዝን ጨምሮ በርካታ የቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ቦታዎች መኖራቸው ጠቁመው፥ ከነዚህም መካከል ትክል ድንጋዮች፣ ፋፋቴዎች፣ ራኮና ባሪቻ ተራራዎች እና ዋሻዎችን ለአብነት አንስተዋል።‎

‎በዞኑ ያለው የሰላም አየር፣ የደራሮ በዓል አከባበር፣ የማህበረሰቡ የእንግዳ አቀባባል፣ ጥምር እርሻና ባህላዊ የምግብ ዝግጅት የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር በማድረግ ዘርፉ እንዲነቃቃ እያደረጉ ያሉ ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ ደርቤ አስረድተዋል።‎

‎ከመጋቢት ወር ጀምሮ የቅርስ አስተዳደር ጽህፈት ቤት በዞኑ ተከፍቷል ያሉት ኃላፊው፥ ቅርሶችን የመንከባከብ፣ የመጠበቅና የማልማት ሥራዎችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመደራጀት እንደሚሠሩ አብራርተዋል።‎

‎የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ጉዳይን ጨምሮ መጸዳጃ ቤቶች፣ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማሟላት የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ልዩ ትኩረት የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።‎

‎በ2018 በጀት ዓመት ላይ ዘርፉን ማነቃቃት ከባህላዊ አስተዳደር ጨምሮ በዞኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን በተለያዩ አማራጮች ለማስተዋውቅ ከሁሉም መዋቅሮች ጋር ተቀናጅተው በትኩረት እንደሚሠሩ አስገንዝበዋል።‎

‎ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ጎበና – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን