ምርት ሲያድግ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል
በደረጀ ጥላሁን
ለሀገራችን የኢኮኖሚ መሠረት በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተውን የግብርና ዘርፍን በዘላቂነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግብርናውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ቴክኖሎጂና ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ አኳያ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በካፋ ዞን የሚገኘው ጊምቦ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና አገልግሎት ማእከል በግብርና ግብአት አቅርቦት ዙሪያ የሚያከናውነውን ተግባር እንደሚከተለው እንቃኛለን፡፡
የጊምቦ ግብርና ግብአትና አገልግሎት ማእከል የተለያዩ ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚያስችሉ የግብርና ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ይታወቃል፡፡
ከነዚህም ግብአቶች ውስጥ ምርጥ የሰብልና የአትክልት ዘሮች፣ የተለያዩ መድሐኒቶች፣ ኬሚካሎች፣ የኬሚካል መርጫ መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች የግብርናውን ሥራ የሚያሳድጉ እና ምርትን የሚጨምሩ ግብአቶች ይገኙበታል፡፡
አቶ አለማየሁ ታደገ የጊምቦ ግብርና ግብአትና አገልግሎት ማእከል ሥራ አስኪያጅ እንዳሉት የማእከሉ መቋቋም ዓላማ አርሶ አደሮች ትክክለኛ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ ግብአት በማቅረብ ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ ይህም አርሶ አደሩ ተመሳስሎ ከሚሰሩና መጠቀሚያ ጊዜያቸው ካለፈባቸው ግብአቶች ተጠብቀው ጥራት ያለውን ግብአት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት አርሶ አደሮች ማእከሉ የሚያቀርባቸውን ግብአቶችን በመጠቀማቸው የሚያመርቱት ምርት አድጓል፡፡ ዋጋው ተመጣጣኝ እና አርሶ አደሩን የማይጎዳ መሆኑን ያወሱት አቶ አለማየሁ ማእከሉ ትርፍን መሰረት በማድረግ ሳይሆን ምርታማነት ላይ በማተኮር የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡
በጊምቦ የግብርና ግብአትና አገልግሎት ማእከል ከአካባው አርሶ አደር በተጨማሪ የተለያዩ አጎራባች ወረዳዎች የሚጠቀሙ ሲሆን የኦሮሚያ አጎራባች ወረዳዎችን ጨምሮ ከዳውሮና ኮንታ አቅራቢያ ያሉ አርሶ አደሮችም የማእከሉን ግልጋሎት እንደሚያገኙ ተመላክቷል፡፡
በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡና ዋጋቻው ዝቅተኛ የሆኑ ግብአቶች በገበያ ውስጥ እንደሚስተዋል የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በተለይ በኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ክልል ድንበር ጎጀብ አካባቢ ችግሩ መስተዋሉን ገልጸዋል፡፡ ይህን የሚመለከተው አካል ከሚያደርገው ቁጥጥር በተጨማሪ በአካባቢው ተጨማሪ ማእከል በመክፈት ችግሩን ለመቅረፍ እቅድ እንደተያዘ ተናግረዋል፡፡
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ደቡብ ማእከል ለጊንቦ ግብርና ግብአት አገልግሎት ማእከል ከምስረታው ጀምሮ እገዛው አልተለየም፡፡ በግብርና ቴክኖሎጂ፣ በቢዝነስ ፕላን፣ በሂሳብ አያያዝ፣ ማናጅመንት እና በሌሎች ለማእከሉ አስፈላጊ የሆኑ ሥልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ አድርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ማእከሉ ሲከፈት ግብአት አሟልቶ ከማስጀመር ሌላ የልምድ ልውውጥ በማስደረግ እንዲሁም ሥራው ዘመናዊ እንዲሆን ድጋፍና ክትትል ማድረጋቸውን ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ግብዓት አቅርቦትና አገልግሎት መስጫ ማእከላትን በመገንባት የአርሶ አደሮችን ምርታማነት፣ እንዲሁም የምግብ ዋስትና እና ገቢን ለማሻሻል እየሰራ የሚገኝ ተቋም በመሆኑ ለጊምቦ ግብርና ግብአት ማእከልም ከፍተኛ ፋይዳ ያለው አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
የግብርና ግብአት ማእከሉ ለወደፊት በተለይ በእንስሳትና እጽዋት ዘርፍ ላይ የተለያዩ ሥራዎች ለመስራት ውጥን መያዙን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ እጽዋትን ለመጠበቅ የሚያስችል የችግኝ ዝግጅት እንዲሁም ሥራውን ይበልጥ ለማስፋፋት አርሶ አደሩን እውቀት በማስጨበጥ ሰፊ ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡
በማእከሉ ከስምንት ሰዎች በላይ የሥራ እድል መፈጠሩን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ አንድ የእንስሳት ሐኪምን ጨምሮ ሁሉም በሥራ ዘርፋቸው የሰለጠኑ ባለሞያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ማእከሉ ከተመሰረተ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በማእከሉ በእንስሳት ሕክምና ላይ እየሰሩ የሚገኙት አቶ አድማሱ ተኮላ የአካባቢው አርሶ አደር በማእከሉ ተጠቃሚ መሆኑን አንስተው ትክክለኛውንና ህጋዊ ግብአቶችን በመጠቀም ምርቱን ማሳደግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው የሰብልና እንስሳት መድሐኒቶች በሕገ ወጥ መንገድ ሲገቡ እንደሚታይ ጠቅሰው ለዚህም ማእከሉ በጉዳቱ ዙሪያ ለተጠቃሚዎች ማብራሪያ በመስጠት ችግሩን ለመፍታት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ሕገ ወጥ ግብአቶችን ባለማወቅ በመጠቀም ብዙ ጉዳት ይደርስ እንደነበር ጠቅሰው በዚህም የከብቶች ሞት፤ በሰብል ምርት አርሶ አደሩ ማግኘት የሚገባውን ምርት ሳያገኝ ይቀር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን የማእከሉ መከፈት ለችግሩ መፍትሄ እየሆነ ይገኛል ብለዋል፡፡
በማእከሉ ግብአት መሸጥ ብቻ ሳይሆን የምክር አገልግሎት ይሰጣል ያሉት ባለሞያው ስለ ግብአት አጠቃቀም አጠቃላይ ገለፃ የሚደረግ ሲሆን በተለይ የኬሚካል አጠቃቀም ጥንቃቄ ስለሚፈልግ ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡
ለህፃናት ያለመሸጥ እንዲሁም ህፃናት በማይደርሱባቸው ቦታዎች ስለሚቀመጡ ኬሚካሎችና መድሀኒቶች ግንዛቤ እንዲያገኙ በስፋት ይሰራል፡፡ ይህ ካልሆነ አርሶ አደሩ ተጎጂ ከመሆኑም በተጨማሪ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይም ችግር ይፈጥራል፡፡ አያይዘውም አጠቃቀሙን በተመለከተ በየቋንቋው ስለሚነገር አብዛኛው አርሶ አደር ተገንዝቦ እየተጠቀመ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ለወደፊት ቢያንስ ሁለት ቦታ ላይ ቅርንጫፍ ለመክፈት እቅድ መኖሩን የገለጹት አቶ አድማሱ ከዚህ በተጨማሪ አንድ የእንስሳት ህክምና ክሊኒክ ለመክፈትም ታቅዷል፡፡ በግብአት አቅርቦት ረገድም የእርሻ መሣሪያዎችን ከግብርና ሜካናይዜሽን ጋር በመነጋገር ለማቅረብ መታቀዱን ነው ባለሞያው የተናገሩት፡፡
አቶ ተወልደብርሀን አለምሰገድ የማእከሉ አግሮኖሚስት እና ሽያጭ ሠራተኛ ናቸው። ማእከሉ በወረዳው ሾምባ በሚባል ስፍራ የራሱን ሰርቶ ማሳያ በማዘጋጀት የአትክልትና የሰብል ዘሮችን በመዝራት ከብቅለት ጀምሮ ሙከራ በማድረግ ለአርሶ አደሩ ያቀርባል። በዚህም አርሶ አደሩን በዘር አዘገጃጀት ላይ የማሰልጠን ሥራ ይሰራል፡፡
ይህን ሰርቶ ማሳያ ለማስፋት ጥያቄ ቀርቦ አበኪቻ በሚባል አካባቢ 26 ሄክታር መሬት በመውሰድ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ለግብርና ኮርፖሬሽን ባለፈው ዓመት 196 ኩንታል የሩዝ ምርጥ ዘር ማስረከባቸውንም አመላክተዋል፡፡
በማእከሉ ለግብይት የሚመጡ አርሶ አደሮች ተመሳስሎ ከሚሰሩ ግብአቶች እንዲጠነቀቁ የሚነገር ሲሆን በማእከሉ የሚቀርቡ ግብአቶች ህጋዊና አስተማማኝ ከሆኑ አቅራቢዎች ስለሚመጣ ዋስትና እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደር አዲስ ሺፈራው በጊምቦ ወረዳ ሸምባ ኪጭብ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ለግብርና ሥራቸው የሚጠቀሙበትን ግብአት ለማግኘት ይቸገሩ ስለነበር እርሻቸውን ያለ ግብአት ለማረስ ይገደዱ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ ይህም የሚያርቱት ምርት አነስተኛና ውጤታማ እንዳይሆን አድርጓል ብለዋል፡፡
ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ጊምቦ ከተማ ላይ ለግብርና ሥራቸው እገዛ የሚያደርግላቸውን ግብአት ለማግኘት የሚረዳቸው የግብርና ግብአት የሚያቀርብ ማእከል ተከፍቶ ሥራ ላይ መዋሉ እፎይታ እንደሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
በአመያ ግብርና ግብአት አገልግሎት ማእከል ለእርሻ ሥራ ግልጋሎት የሚውሉ እና የእርሻ ምርትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ግብአቶች የሚቀርቡ ሲሆን አርሶ አደር አዲስም ከማእከሉ ምርጥ ዘር፣ የእንስሳት እና የሰብል መድሐኒቶች፣ ኬሚካሎችና ሌሎች ግብአቶችን በመግዛት እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ግብአቶች ለእርሻ ሥራቸው በፈለጉት ጊዜ እና መጠን ማግኘት በመቻላቸውም ደስተኛ ናቸው፡፡
ዋጋውም ቢሆን ተመጣጣኝና ከጥቅሙ አንፃር የማይጎዳ መሆኑን የተናገሩት አርሶ አደር አዲስ ግብአት ተጠቅሞ የግብርና ሥራን መስራት ምርትን የሚጨምር በመሆኑ ውጤቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ለአርሶ አደሮች ምርትን ሊያሳድጉ የሚችሉ በቂ ግብአቶችን በማቅረብ የምግብ ዋስትናችንን በዘላቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
More Stories
“በመምህርነቴ የሚሰማኝ እርካታ ከፍተኛ ነው” – መምህር ቆስቲ ስማ
“አካል ጉዳተኝነት ህይወትን በሌላ መልኩ መኖር መቻል ነው” – ወጣት ታምራት አማረ
ትንሽ ዕድሜ፤ ትልቅ ዓላማ