በመትከል ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ሀገራዊ ጥሪ እንሰለፍ!

በመትከል ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ሀገራዊ ጥሪ እንሰለፍ!

በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ በሀገራችን የተረጋጋ ሀገርና ትውልድ ለመገንባት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት መርሃ ግብሩ ከተበሰረ ወዲህ በተለያዩ ዘርፎችም መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ የሀገራችን የደን ሽፋን መጠንም በፍጥነት እየተቀየረ መጥቷል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የታጀበው ሰባት ዓመታትን የተሻገረ የአትዮጵያ ብልጽግና ጉዞም በሀገራችን ከፍተኛ ውጤቶችን ከማሳየት ባለፈ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ተቋማት ተጽዕኖ ፈጣሪነት ደረጃዋን ከፍ አደርጓታል፡፡

በመረሃ ግብሩ የዕድሜ፣ የፆታ፣ የብሔር፣ የሃይማኖትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይስተዋሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሕብረተሰብ ክፍሎች በስፋት በመሳተፍ አይተኬ ተሳትፎ አደርጓል፡፡

በሂደቱም መላው ሕዝባችን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግና ለውጤት ማብቃት ባደረገው የጋራ ርብርብ ዘርፈ-ብዙ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ ያሳካን እምርታ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ከቆምንና ከተባበርን ተዓምራዊ ስራዎችን መከወን እንደምንችል ያሳዩ ናቸው፡፡

የኑሮ መሠረታችን አረንጓዴ ተክሎች መሆናቸውን ሕዝባችን ከመረዳት ባለፈ በተግባር አስመስክሯል፡፡ በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት በከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ከ40 ቢሊዬን የሚልቁ ችግኞችን እንደ ሀገር ታቅዶ ተተክሏል፡፡ በዘንድሮው ክረምትም 7.5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

የተተከሉ ችግኞች የማህበረሰቡ የባለቤትነት ስሜትን እና ለአካባቢው ሃላፊነትን እየጎለበቱ በመምጣቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ፣ የአፈር መሸርሸርን ከመቀነስ፣ የደን ሽፋንን ከማሳደግ፣ ለአየር ሚዛን ጥበቃ እና ሕይወት ላለው ሁሉ ለመኖር ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ለአከባቢና ሀገር ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አበርክቶ እያደረገ ይገኛል፡፡

ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአንድ ቀን ሰባት መቶ ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል በዚህ ክረምት ለማሳካት የታቀደውን 7.5 ቢሊዮን ግብ እውን እንድናደርግ ዐሻራችንን እንድናኖር ለመላው ኢትዮጵያዊያን ጥሪ ቀርቧል።

ስለሆነም መላ ሕዝባችን ከሁሉም ኢትዮጵያ ማዕዘናት ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ/ም በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዬን ችግኝ በመትከል የታቀደውን ግብ እንድናሳካ ሀገራዊ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በሁሉም ሀገራችን ክፍሎች በርካታ ዜጎች እንዲሳተፉ በማድረግ ለሀገራችን ማንሰራራት ዐሻራችንን ማኖር ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን ስናደርግ የሀገራችን የተፈጥሮ ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነታችንን እናረጋግጣለን፡፡

ለቀረበው ታሪካዊና ሀገራዊ ጥሪ ተግባራዊነት በመዘጋጀትና ምላሽ በመስጠት የኢትዮጵያን መንሰራራት ጅምር እውን በማድረግና የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅበትን አስተዋጾኦ እንዲያበረክት መንግስት ዳግም ጥሪውን ያቀርባል።

በመትከል እናንሰራራለን!

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት