የግብርና ዘርፍ የእሴት ሰንሰለትን በመከተል የስራ ዕድልን መፍጠር በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለፀ
ይህ የተገለፀው በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በአደይ ፕሮግራም ድጋፍ በከምባታ ዞን የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የመኸር ስንዴ ሰብል ዘር ማስጀመሪያና የድንች ሰብል ማሳ እንዲሁም የዶሮ እርባታና ጥምር ግብርና የመስክ ምልከታ በተካሄደበት ወቅት ነው።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በግብርና ተኮር ዘላቂ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም የሚሳተፈው አደይ ፕሮግራም በክልሉ በ15 ወረዳዎች ላይ እንደሚሰራና ከእነዚህም በከምባታ ዞን የሚገኙ ወረዳዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የግብርና ዘርፍ የእሴት ሰንሰለትን በመከተል የስራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዝ እንደሆነ በማንሳት ፕሮግራሙ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከተረጂነት በመላቀቅ የተሟላ የኢኮኖሚ ሉአላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል።
በከምባታ ዞን በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ኢንተርፕራይዞችም የዚሁ ሪፎርም አካል እንደሆኑ በማመላከት፤ በዘርፉ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ወጣቶች የተሻለ ምርት እንዲያገኙ ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። ሌሎች ወጣቶችም ከእነሱ ተሞክሮ በመውሰድ ወደ ተግባር እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአደይ ፕሮግራም በክልሉ ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራን በማገዝ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በተለይም ፕሮግራሙ ለኢንተርፕራይዞች የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ የምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ለዘርፉ ውጤታማነት በየደረጃው ያለውን አመራር መደገፍ እንዳለበት በመጥቀስ ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው በዞኑ ስራ አጥ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመው የአደይ ፕሮግራም ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የስልጠናና የግብዓት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ይህም ምርታማነትን በማሳደግ ወጣቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል ያሉት ዋና አስዳዳሪው፤ በዘርፉ የተጀመረው ስራ ውጤታማ እንዲሆንም በየደረጃው እየተደረገ ያለው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ተኮር ዘላቂ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም (አደይ) ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አለሙ ተከተል እንደገለፁት፤ ኢንስቲትዩቱ በክልሉ የግብርና ምርታማነትን ሊያዘምኑ የሚችሉ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝና ከእነዚህም መካከል በአደይ ፕሮግራም የሚከናወነው ግብርና ተኮር የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም አንዱ ነው።
አክለውም በዘርፉ የሚደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች 80 በመቶ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ የተቀሩት 20 በመቶ ወንዶች መሆናቸውን በመግለፅ ወጣቶቹ በእንሰሳት፣ በሰብል ልማት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በገበያ ትስስር እና በመሠል ዘርፎች እንደሚሰማሩ ጠቅሰዋል።
በክልሉ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በ15 ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ 11 ሺህ ለሚሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች የክህሎት ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው፤ ይህንኑ ተከትሎም ወጣቶቹ ወደ ስራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በ3 ወረዳዎች ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች 250 ኩንታል ድንች በዘር ብዜት ተደራሽ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
የከምባታ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ መልካሙ ማቲዎስ እንዳሉት፤ በዞኑ የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ ስራ እየተሰራ ይገኛል።
ለዘርፉ ውጤታማነት በየደረጃው በሚደረገው ጥረትም የአደይ ፕሮግራም ትልቅ ዕገዛ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በተካሄደው የመስክ ምልከታም ተስፉ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏልም ነው ያሉት።
በዞኑ በሁሉም የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ በመግለፅ ለስኬታማነቱም ሁሉም ማገዝ እንዳለበት ተናግረዋል።
በአደይ ፕሮግራም የታቀፉ ኢንተርፕራይዞች አባላት በሰጡት አስተያየትም፤ ተደራጅተው ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ ለመሆን ጠንክረው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የአደይ ፕሮግራም የክህሎት ስልጠናና የግብአት አቅርቦት ድጋፍ እንዳደረገላቸው የተናገሩት ወጣቶቹ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በኩልም የመሬት እና መሠል ድጋፎች እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቀጣይም ጠንክረው በመስራት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ውጥን እንዳላቸው በመጠቆም፤ በየደረጃው እየተደረገላቸው የሚገኘውን ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የግብርና ዘርፍ የእሴት ሰንሰለትን በመከተል የስራ ዕድልን መፍጠር በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለፀ
በጥረቱ ውጤታማ የሆነው ወጣት ተሞክሮ!
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ነገ ሐምሌ 24/2017 “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሔደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ የክልሉ ህዝብ የላቀ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ