በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በደቡብ ኣሪ ኮመር ቀበሌ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የዕለት ደራሽ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ
ሰብአዊ ድጋፉ በክልሉ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አማካይነት የተሰባሰበ ስለመሆኑም ተመላክቷል።
ሰሞኑን በኣሪ ዞን በደቡብ ኣሪ ወረዳ ኮመር ቀበሌ የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመጀመሪያ ዙር ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
በክልሉ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹ ማለትም ከጎፋ፣ ወላይታና ጌዴኦ ቅርንጫፎች የተሰባሰበ ድጋፍ በክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በቀጥታ ለተጎጃዎቹ መቅረቡን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀይ መስቀል የሰብአዊ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ሙሉዋስ አቲሳ አስታውቀዋል።
በተቀናጀ መልኩ ድጋፍ ከተደረጉ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች መካከል በአደጋው ለተፈናቀሉ ወገኖች የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ የንጽህና መጠበቂያዎች፣ ብርድ ልብሶችን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች የተካተቱበት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በድንገተኛ አደጋዎች ወቅት በፈጥኖ ደራሽ ሰብዓዊ ተግባራቱ የሚታወቀው ማህበሩ በመጀመሪያ ዙር ካደረገው ድጋፍ ባሻገር በቀጣይ ሌሎች መሰል ድጋፎችን በቀሪ ቅርንጫፎቹና በብሄራዊ ማህበሩ በኩል ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አቶ ሙሉዋስ ገልጸዋል።
በማህበሩ የደቡብ ኦሞ ዞን ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ቢሻው፤ አደጋው ከተከሰተበት ወቅት ጀምሮ አስክሬን በማፈላለግና አስፈላጊ ድጋፎችን በማቅረብና በማስተባበር ሰፊ ሰብዓዊ ድጋፎች ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ላደረገው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በደቡብ ኣሪ ዞን በአደጋው ከሟች ቤተቦች በተጨማሪ በርካታ የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን በመጥቀስ በተለያዩ መዋቅሮች እየተደረገ ያለው ወገናዊ አጋርነት የሚያስመሰግን መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኣሪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ግዛው ኃይሌ ናቸው።
ዘጋቢ፡ ወንድማገኝ በቀለ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ግብር ለከተማው ብሎም ለሀገር ልማት ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ለደንበኞቻቸው ደረሰኝ በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውን በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ግብር ከፋዮች ተናገሩ
ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ገለፀ
ገቢ ከራስ ለራስ የሚዉል በመሆኑ በቴክኖሎጂ በተደገፈ የአከፋፈል ስርዓት በአጭር ቀናት ከታቀደው በላይ ግብር መሰብሰብ እንደሚገባ ተገለጸ