የማሻ ከተማ የእግር ተጓዥ ወጣቶች ማህበር በአከባቢው የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፋራዎችን ጎበኙ

የማሻ ከተማ የእግር ተጓዥ ወጣቶች ማህበር በአከባቢው የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፋራዎችን ጎበኙ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማሻ ከተማ የእግር ተጓዥ ወጣቶች ማህበር በአከባቢው የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፋራዎችን በመጎብኘት የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን አውቀን ለአለም እናሳውቅ በሚል መሪ ሀሳብ በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ ኬዎ ቀበሌ ያለውን የጋሀማዎ ፏፏቴ ጎብኝቷል።

የኬዎ ቀበሌ ነዋሪዎች ላደረጉት ደማቅ አቀባበልና ላሳዩት መልካም ትብብር ምስጋናቸውን ያቀረቡት ወጣቶቹ፥ አካባቢያቸውን ለማወቅ የጀመሩትን ጉዞ በማጠናከር ሸካን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ትኩረት እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።

የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን አውቀን ለአለም እናሳውቅ በሚል መሪ ሀሳብ የማሻ ከተማ የእግር ተጓዥ ወጣቶች ማህበር በሸካ ዞን ውስጥ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ተዘዋውረው ለመመልከት ማቀዳቸው ተመላክቷል።

ከማሻ ከተማ 27 ኪሎ ሜትር፣ ከይና ቀበሌ 9 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከዞን ዋና ከተማ ቴፒ 78 ኪሎ ሜትር ርቀው በማሻ ወረዳ ኬዎ ቀበሌ የሚገኘው የጋሀማዎ ፏፏቴ የወጣቶቹ መዳረሻ መሆኑን ተጠቁሟል።

ፏፏቴው ስያሜውን ያገኘው “ጋሆ” እና “ማሆ” ከሚባል ሁለት የሸክኖኖ ቃላት ሲሆን፥ ጋሀማዎ ማለት ጎሽ በላ የሚል ትርጉም የሚሰጥና ፏፏቴው በድሮ ዘመን ጎሽ እንደበላ ወይም በወንዙ ውስጥ ጎሽ ሙቶ እንደተገኘ የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።

የጋሀማዎ ፏፏቴ በነጎድጓድ ድምፁ ነጭ ፈትል ሸማ ለባሽነቱ በአረንጓዴው መስክ መንጣቱ በውርጩ ዙርያ ገባውን ማረስረሱ ልዩ ውበት በመፍጠር የተመልካቹን ቀልብ የመያዝ አቅም አለው።

አካባቢው በተፈጥሮ ያሸበረቀ እና በጥብቅ ደን የተከበበ በመሆኑ ለቱሪዝም መስህብነት ማራኪ የሆነ ስፍራ ቢሆንም፤ ይህን ልዩ ተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የመንገድ መሰረተ ልማት ማሟላት ላይ ቀጣይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ነው ወጣቶቹ የሚገልጹት።

በጉዟቸው አካባቢያቸው ላይ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ማወቅና ለሌሎች ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን አላማቸው በቦታው በመገኘት በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች አንድነታቸውን እያጠናከሩ የማይረሳ ጊዜ ማሳለፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ድንቅ የተፈጥሮ ሀብት ሁሉም የሀገራችን ዜጎች መጎብኘት እንዳለባቸው የጠቆሙት ወጣቶቹ፥ የሚመጡ ቱሪስቶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ወንድማገኝ ገሪቶ – ከማሻ ጣቢያችን