ግብር ለከተማው ብሎም ለሀገር ልማት ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ለደንበኞቻቸው ደረሰኝ በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውን በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ግብር ከፋዮች ተናገሩ

ግብር ለከተማው ብሎም ለሀገር ልማት ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ለደንበኞቻቸው ደረሰኝ በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውን በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ግብር ከፋዮች ተናገሩ

ደረሰኝ መስጠትም ሆነ መቀበል ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን ለማጎልበት ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑን የይርጋጨፌ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

አቶ ሁሴን ሀሰን እና ቴዎድሮስ ፈቃዱ በከተማው በሸቀጣ ሸቀጦችና በህንፃ መሳሪያ ንግድ ሥራ የተሰማሩ ደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ሲሆኑ ግብር ከንግግር ባለፈ ሀገርን በተግባር የመውደድ መገለጫ በመሆኑ የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማው የሚታዩ አዳዲስ የመሠረተ ልማት አውታሮች መንግስት የሚሰበሰበውን ግብር በተግባር እያዋለ ስለመሆኑ አመላካች መሆኑን የተናገሩት ግብር ከፋዮቹ፤ ለደንበኞቻቸው ደረሰኝ በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውን ግብር ከፋዮች ተናግረዋል።

ደረሰኝ የማግኘት ችግር መኖሩን እና ይህም በህጋዊው የንግድ ስራቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያደረገ በመሆኑ በሚመልከታቸው አካላት ሊቀረፍ እንደሚገባ ግብር ከፋዮች አሳስበዋል።

ለገዙት ዕቃ ከሻጩ ደረሰኝ ጠይቆ የሚቀበልና ህጋዊ መብቱን የሚያስከብር ማህበረሰብ ለመፍጠር በተሠራ ሥራ አሁን ላይ ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መሆኑን የተናገሩት በከተማው ገቢዎች ጽ/ቤት የምጣኔ ጥናት፣ የታክሲ ትምህርትና ቅሬታ አጣሪ አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ሰንበቶ ናቸው።

ከደረሰኝ አሰጣጥና አቀባበል ጋር ተያይዞ የሚፈጥሩ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅርቡ ተሻሽሎ በወጣ ህግ መሠረት የገንዘብና የእስራት እርምጃ አወሳሰድ በተመለከተ ለነጋዴ ማህበረሰብና ሰዎች በሚበዛባቸው አካባቢዎች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሠራቱን አስተባባሪው ጠቁመዋል።

የይርጋጨፌ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ ከበደ በከተማው በተጨባጭ የልማት ጅምሮችን ለማስቀጠል በትኩረት እየሠሩ እንደሆነ በመግለፅ የVAT እና የTOT ተመዝጋቢ ሆነው ደረሰኝ በማይሰጡ የንግድ ተቋማት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልፀው፤ እርምጃውም ከ10 ሺህ እስከ 100 ሺህ የገንዘብ እና ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት መሆኑን አክለዋል።

የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው ለግብር ሕግ ተገዢ በመሆን፣ ደረሰኝ በመስጠትና በመቀበል ግብይት በህግ አግባብ ሲፈጸም ብቻ በመሆኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተገቢው ለመመለስ ነጋዴዎችና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ኃላፈው አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን