ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ገለፀ

ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ገለፀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታውቋል፡፡

መምሪያው ባለፉት አምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የ2017 የደረጀ “ሐ” ግብር አሰባሰብ መጠናቀቁን አመላክቷል።

የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚነወር ሀያቱ የበጀት አመቱ እቅድ አፈጻጸምን አስመልክተው እንዳሉት በበጀት አመቱ ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 3 ቢሊዮን 672 ሚሊዮን 186 ሺህ 772 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በእስካሁኑ ሂደት 3 ቢሊዮን 232 ሚሊዮን 25 ሺህ 404 ብር መሰብሰብ ተችሏል።

አፈጻጸሙ የተሻለ እንዲሆን የታክስ መሰረት የማስፋት፣ ከ2ሺህ 400 በላይ አዳዲስ ግብር ከፋዮች ወደ ግብር ማዕቀፍ የማስገባት፣ የግንዛቤ ስራ የመስራት፣ የገጠር መሬት አዋጅ ግብር አሰባሰብ፣ የታክስ ህግ ተገዢነት ስራ የመስራትና የፊት አመራሩና የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በበጀት አመቱ ግብር ከፋዩ ለታክስ ህግ ተገዢ ያለመሆን፣ ግብይት በደረሰኝ ያለመፈጸምና በሀሰተኛ ደረሰኝ ማቀናነስ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ያነሱት ኃላፊው፥ በዚህም የታክስ ህግ ተገዢነት በተላለፉ 122 ግብር ከፋዮች ላይ የ6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ቅጣት መጣሉን አመላክተዋል።

የታክስ መሰረትን በማስፋት ከተሰሩ ስራዎች መካከል አንዱ የገጠር መሬት አዋጅ ግብር መሆኑን የገለጹት አቶ ሚነወር በዚህም ከ160 ሺህ አርሶ አደሮች 220 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም አስረድተዋል።

በበጀት አመቱ 46 ግብር ከፋዮች ቅሬታ አቅርበው 44ቱ ቅሬታዎች በአግባቡ እንዲፈቱ መደረጉን ጠቁመው 2ቱ በሂደት ላይ መሆናቸውንም ኃላፊው አውስተዋል።

በዞኑ 17 ሺህ 66 የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መኖራቸውን አንስተው በእስካሁኑ 16 ሺህ 881 ግብር ከፋዮች መክፈላቸውን በመጠቆም ከነዚህም 81 ሚሊዮን 96 ሺህ 663 ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም ሊሳካ የቻለው በአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠቱ፣ የመረጃ አሰባሰብ ስራ መሰራቱ፣ ከግብር ከፋዮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተሰሩ ስራዎችና ግብር ከፋዮች በቴሌብር ጭምር እንዲከፍሉ በመደረጉ መሆኑን አመላክተዋል።

በዞኑ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማከናወን ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

ግብር ከራስ ወስዶ ለራስ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሚነወር ግብር ከፋዮች ግብይት በደረሰኝ ከመፈጸም ባለፈ ካገኙት ገቢ ግብርን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

አክለውም በበጀት ዓመቱ የአመራር ስልቶችን በመጠቀም በበጀት ዓመቱ የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን መቻሉን ገልጸው፥ የደረጀ “ሐ” ግብር ከፋዮች በተገለጸው ጊዜ ሰሌዳ ግብራቸውን በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን ለተወጡ ለነጋዴው ማህበረሰብ በሙሉ እንዲሁም በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዞኑ 497 የደረጃ “ለ” እና 940 የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች መኖራቸውን አንስተው፥ ሁሉም ግብር ከፋዮች ካገኙት ገቢ በወቅቱና በታማኝነት ግብራቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉም አቶ ሚነወር ጥሪ አቅርበዋል።

በዞኑ በወልቂጤ ከተማ አግኝተን ያነጋገርናቸው ግብር ከፋዮች በሰጡት አሰተያየት ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈላቸው እውቅና እንዳገኙ አንስተው ይህም ለቀጣይ መነሳሳትን እንደሚፈጠርላቸው ተናግረዋል።

ግብር መክፈል ግዴታም ጭምር ነው ያሉት ግብር ከፋዮቹ የከፈልነው ግብር ተመልሶ ለራሳችን መሰረተ ልማቶች ይውላል ሲሉ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን