የውቅሮዋ ልብስ ሰፊ
በደረሰ አስፋው
የዛሬ 11 ዓመት ወደ ሀዋሳ ሲመጡ ስራ አልነበራቸውም፡፡ ሰርተው ለመለወጥ በሚል እንጂ፡፡ ባለቤታቸው ቀድመው ሀዋሣ ቢመጡም ዘወትር ስራ ባለማግኘት ግን ይፈተኑ ነበር፡፡ አንድ ቀን ስራ ካገኙ አብዛኛውን ቀን ግን ከስራ ውጪ ይሆኑ ነበር። የባልን እጅ እያዩ ለሚኖሩት የቤት እመቤት ኃላፊነቱ የገዘፈ ሆነ፡፡ ከቤት ወጥተው ስራ ፍለጋ የሀዋሳ ከተማን ቢቃኙም አልተሳካም፡፡ የቀበሌና ክፍለ ከተሞችን ቢሮዎች ቢጎበኙም አልተሳካም፡፡
የቤት ክራይና ቀለብ ደግሞ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሰርቼ እለወጥባታለሁ ያሏት ሀዋሳ ከተማም ስራን ነፈገቻቸው፡፡ ጉልበትና ጤና እያላቸው ሰርተው ኑሯቸውን መደጎም አለመቻላቸውም ቁጭት ውስጥ ከተታቸው፡፡ ምን ቢሰሩ ከዚህ ቁጭት እንደሚያወጣቸውም ማሰብ ጀመሩ፡፡
ድንገት ስራ ፍለጋ ብለው ከቤት ወጡ፡፡ እግረ መንገዳቸውን ወደ አንዱ ልብስ ስፌት ጎራ ማለታቸው አልቀረም፡፡ ጎራ ያሉበት ልብስ ቤት የተመለከቱት ምርጫቸው አደረጉት፡፡ ወደ ተግባር ለመግባት ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ በእጅ ካለው ላይ ተጨማሪ ብድር ወስደው የልብስ ስፌት ማሽን (ሲንጀር) ገዙ፡፡ ማሽኑን ይግዙ እንጂ የሙያው እውቀትም ይሁን ልምዱ ግን አልነበራቸውም፡፡ ለዚህም በቤት ውስጥ ለ6 ወራት መለማመድ ሆነ፡፡
ከ6 ወር በኋላ ከማሽኑ ጋር እጅና ጓንት ሆኑ፡፡ እግራቸው አይደለም እጃቸውም መቀስ ይዞ ለመቁረጥ ድፍረቱን አገኘ፡፡ የቤት እና የጎረቤትን ልብስ በመስፋት በስራው በቂ ክህሎትን ጨበጡ፡፡ ይህም ከቤት ወጥተው ዛሬ ላይ በሚሰፋበት ቦታ ተቀምጠው እንዲሰፉ ድፍረት ሰጣቸው፡፡ በዚህ ሙያ ከ10 ዓመታት የተሻገረ ልምድንም እንዳካበቱ ነው የገለጹት፡፡
ያገኘናቸው በስራ ቦታቸው ላይ እያሉ ነው። ችግር ካልገጠመ በስተቀር እንደማንኛውም ሰራተኛ ሰአታቸውን ጠብቀው በስፍራቸው እንደሚገኙ ነው የገለጹልን፡፡ በርካታ ደንበኞችን አፍርተዋል፡፡ አሁን ላይ ማንኛውንም የልብስ አይነት እንደሚሰፉም ነው የገለጹልን፡፡ አልችልም የሚል ነገር እንደሌለም በመግለጽ፡፡ ሙያውንም በልምድ እንጂ የሙያ ማሰልጠኛ ገብተው ያዳበሩት አለመሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ወ/ሮ በላይነሽ ዳና ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ ከተማ ውቅሮ ቀበሌ በተለምዶ ጎድጓዳ ሰፈር ነዋሪ ናቸው፡፡ የተወለዱት ወላይታ ዞን ገሱባ ወረዳ ሳዶይ ቀበሌ ነው፡፡ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ከእኩዮቻቸው ጋር በመንደራቸው አፈር ፈጭተው ጭቃ አቡክተው ተጫውተዋል፡፡ ውሃ ቀድተው፣ እንጨት ለቅመው፣ ከብት ጠብቀውና በቤት ውስጥ ስራ ቤተሰባቸውን በማገዝ አድገዋል፡፡
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በአካባቢያቸው በሚገኝ ዋረዛ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ በልጅነታቸው ኮሊጅ ገብተው ዲግሪ ይዘው የመንግስት ሰራተኛ እሆናለው የሚለው ምኞታቸው ግን በመሀል መክኖ ቀረ። ልጅሽን ለልጄ ተብለው የተጠየቁት ቤተሰቦች በልጃቸው ላይ ጫና በመፍጠር ከትምህርት ይልቅ ትዳር እንዲመሰርቱ አደረጉ፡፡ ከትምህርቱ ይልቅ ዝምድናን ሊጨምሩ ወልደው ዘርን ሊያበዙ ተመኙ፡፡
ከትዳር በኋላ ጎጆ ቀልሰው የራሳቸውን ህይወት መምራት ጀመሩ፡፡ ግብርና ስራም የኑሯቸው መተዳደሪያ ሆነ፡፡ ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቀው የራሳቸውን ህይወት መምራትም እንዲሁ ቀላል አልነበረም፡፡ የባልን እጅ እያዩ የጨው፣ በርበሬና የዘይት እያሉ መኖር ልማዳቸው አደረጉ፡፡ ይሁን እንጂ ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሮ ለትዳር አጋራቸውም ምቾትን የነፈጋቸው ሆነ፡፡ ይህን ታሪክ ለመለወጥ ብቸኛ ምርጫቸው ያደረጉት ስራ ፍለጋ በሚል ወደ ከተማ መሰደድን ነው። የትዳራቸው አጋር የሆኑትን ወ/ሮ በላይነሽን ገጠር ትተው ሀዋሳ መጡ፡፡
በ2006 ዓ.ም ወ/ሮ በላይነሽ ወደ ሀዋሳ መምጣታቸው አልቀረም፡፡ ሀዋሳ ከተማ መጥተው ኑሮ የዋዛ አልሆነላቸውም፡፡ ባለቤታቸው በሚያገኙት የቀን ስራ ገቢ ብቻ መተዳደር ሆነ፡፡ በቀን የሚያገኙት 80 ብር ለእለት ወጪዎች፣ ለቤት ክራይ፣ የቀለብ፣ በመንደሩ ለሚከሰት ለሀዘንም ይሁን ለደስታ የማህበራዊ ጉዳዮች ሲመነዘር ጫናው በሳቸው ላይ ብቻ የወደቀ ሆነ፡፡ ችግርን መጋፈጥ ግድ አላቸው፡፡
ወ/ሮ በላይነሽ በዚህ ጊዜ ቤት ቁጭ ማለቱ እረፍት ነሳቸው፡፡ ለከተማው እንግዳ ቢሆኑም በድፍረት እግር ወደመራቸው የቀን ስራ ፍለጋ መውጣታቸው አልቀረም፡፡ በቀበሌ እና ክፍለ ከተማ አካባቢም ተንቀሳቅሰው ስራ ለማግኘት ሞክረው ነበር፡፡ አንዳንዶች ተስፋ ቢሰጧቸውም የሚጨበጥ ነገር ግን አልነበረም፡፡
2006 ዓ.ም ወደ ልብስ ስፌት ሙያ እንዲገቡ ተመኙ፡፡ ድንገት የተቀደደ ልብስ ለማሰፋት በሄዱበት ይህን እኔም ባደርግ የሚለው ሀሳብ ወደ ውስጣቸው መጣ፡፡ ጊዜ ሳይወስዱ ከባለቤታቸው ጋር ተማከሩ፡፡ አሮጌ የልብስ ስፌት ማሽን (ሲንጀር) በ6 ሺህ ብር ገዙ፡፡ ይህን ሲያደርጉ የነገን በማሰብ እንጂ በሙያው ልምዱ አልነበራቸውም፡፡
ይህን ማሽን ገዝተው በቤት ውስጥ በእግር በማንቀሳቀስ ለ6 ወር መቆየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በቤት ውስጥ የራሳቸውንም ሆነ የልጆችን ልብስ መስፋት አለፍ ሲልም የጎረቤትን ልብስ በመስፋት ከማሽኑ ጋር ተለማመዱ፡፡ አሮጌ የተቀደዱ ልብሶችን ከመስፋት አለፍ ያለ ልምድ አዳበሩ፡፡ ከዚህ በኋላ በቤት ውስጥ ሳይሆን ውጪም ቢወጣ ሙሉ የሚያደርግ እውቀት ጨብጫለሁ በማለት ዛሬ በሚሰፉበት ቦታ እንደወጡ አጫወቱኝ፡፡
ዛሬ በስፍራው ላይ ተገኝቼ ባነጋገርኳቸው ወቅት መለስ ብለው ከዛሬ 11 ዓመት በፊት የነበረውን የኑሮ ጫና ነው ያስታወሱኝ፡፡ ይህን ችግር አሸንፎ ለመውጣት ያለፉበትን ውጣ ውረድም አልዘነጉትም፡፡ ካለስራ መኖር ህይወት እንደሚያጎሳቁል የተገነዘቡበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ ይህን ችግር በስራ አሸንፈው ታሪክ አድርገውታል፡፡
በፈጠሩት ስራ ህይወታቸው ከቀድሞው ተለውጧል፡፡ በዚሁ ስራ 4 ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው 12ኛ ክፍል ተፈታኝ ነው፣ ሌላው ወደ 12ኛ ክፍል ያልፋል። ሌላኛው 9ኛ ክፍል ሲሆን የመጨረሻ ልጃቸው ደግሞ 7ኛ ክፍል ነው፡፡ እነዚህን በማስተማር ለቁም ነገር ለማድረስ ይተጋሉ። የባልን እጅ ጠብቀው ከሚኖሩበት ህይወት ወጥተዋል፤ ጓዳቸው ሙሉ ነው፡፡ ከወርሃዊ ቀለብ ውጪ አብዛኛውን ወጫቸውንና ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን የሚሸፍኑት በዚሁ የልብስ ስፌት ስራቸው ነው፡፡ የቤት ክራይም የሚከፍሉት ከዚሁ ነው፡፡
“የፍላጎት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሌሎች ሴቶችም በዚህ ስራ ቢሰማሩ አዋጭ ነው፡፡ በተለይ በቤት ውስጥ ለምትኖር ሴት ችግርን የማሸነፊያው መንገድ ስራ በመሆኑ ወጥተው እንዲሰሩ እመክራለሁ፡፡ መስራት የወንድን እጅ እያዩ ከመኖርም ይታደጋል፡፡ ቤተሰብን በተገቢው ለመምራት ይረዳል፡፡ ለሀገርም ጠቃሚ ነው” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
“ምንም እንኳ ከጓዳ የዘለለ የሚታይ ሀብት ባልፈጥርም የሰው እጅ ከማየት አድኖኛል፡፡ ከኔም አልፌ በሙያዬ ልጆቼንም አስተምሬያለሁ፡፡ በሌለሁ ጊዜ እየሰሩ የራሳቸውን የትምህርት ቤት የደብተር፣ እስክርቢቶና የትምህርት ቤት የደንብ ልብሳቸውን ወጪ ይሸፍናሉ፡፡
አሁን ላይ ባካበቱት ልምድ አዳዲስ ልብሶችን ቀደው መስፋት ይችላሉ፡፡ የሴቶች ቱታ ቢሆን የወንዶች ቁምጣ ይሰራሉ፡፡ የተማሪዎችን የደንብ ልብስ ቀደው ይሰፋሉ፡፡ እጅ ስላጠራቸው እንጂ ልብስ ቤት ከፍተው ስራቸውን የማስፋት ብሎም የማዘመን ውጥን ሁሉ አላቸው፡፡ ይህንንም እንደሚያደርጉት ነው በሙሉ እምነት የሚናገሩት፡፡
ደንበኞቻቸው ያበረታቷቸዋል፡፡ አላፊ አግዳሚው በዚህ ስራ ላይ ሆነው ሲመለከቷቸው ያደንቋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ጉልበት እንደሆናቸው ገልጸው ነገን አርቀው እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው ነው የተናገሩት፡፡ ከዚህ ባለፈ ሰርተው ከሚያገኙት እቁብ ይጥላሉ፡፡ ይቆጥባሉ፡፡ በሳምንት እስከ 6 ሺህ ብር እንደሚቆጥቡም ነው የተናገሩት፡፡ ወ/ሮ በላይነሽ መነሻ የሚሆን ብር ካገኙ ልብስ ቤት የመክፈትና ጎን ለጎን ሌሎች ስራዎችንም የመስራት ሀሳብ አላቸው፡፡
More Stories
“አካል ጉዳተኝነት ምንም ነገር ከማድረግ አያግድም” – ወጣት አብዱል ሀቅ ሙክሲን
የዕልፍ ውበት መገኛ ሥፍራ
“እየሠራን እዚያው መኖር ከባድ ነው” – ወ/ሮ ዘነበች ደምሴ