ከደም ተዋፅኦ መድኃኒት በማምረት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ የደም መድኃኒቶችን ለማምረት እየተሰራ ይገኛል – የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት

ከደም ተዋፅኦ መድኃኒት በማምረት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ የደም መድኃኒቶችን ለማምረት እየተሰራ ይገኛል – የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት

‎ከደም ተዋፅኦ መድኃኒት በማምረት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ የደም መድኃኒቶችን ለማምረት እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ የበጎ ፍቃድ ደም ለጋሾች እና ተቋማት የምስጋና እና የዕውቅና መርሀ ግብር በወላይታ ሶዶ ተከናውኗል፡፡

‎የብሄራዊ ደም ባንክ ደምና ህብረ ህዋስ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ጤናዬ ደስታ እንዳሉት፤ የሚቀዳ ደም ጥራቱና ደህንነቱ እንዲረጋገጥ የደም መመርመሪያ ማሽን አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ለማሳካት የመመርመርያ ማሽን የሟሟላት ስራ ይሰራል።

‎ቋሚ ደም ለጋሾች ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ አንድ ሰው አንዴ ከለገሰ የ4 ሰዎችን ህይወት ስለሚታደግ ሁሉም አካላት በተነሳሽነት መንፈስ ደም መለገስ እንዳለበትም አሳስበዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በክልሉ ደም ከመለገስ አንፃር ለውጦች ቢኖሩም ባህል ከማድረግ አንፃር ክፍተቶች መኖራቸውን አውስተው፤ ቋሚ ለጋሾችን ከማፍራት አንፃርም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አብራርተዋል።

‎አክለውም የክትትልና የድጋፍ እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራርን በማስፈን በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ የደም ባንኮችን የመደገፍ ስራ በቅንጅትና በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ወላይቴ ቢተው ባለፉት ጊዜያት በክልሉ ደም ለመለገስ የተደረገው ቁርጠኛ እንቅስቃሴ ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለው፤ በቀጣይም ዋጋው ውድ የሆነውን ደም በሚፈለገው ልክ ለማሰባሰብ መስራት ያሻል ሲሉ ጠቁመዋል።

‎በደም እጦት ህይወታቸውን እያጡ የሚገኙ ወገኖቻችንን ለመታደግ በቅንጅት መስራት ያሻል ያሉት ወ/ሮ ወላይቴ፤ እንደህዝብ ተወካይነታችን በቀጣይ ውጤት የሚያመጡ የቁጥጥር፣ ክትትልና የድጋፍ ስራዎችን እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

‎በመርሀ ግብሩ የበጎ ፍቃድ ደም ለጋሽ ተቋማት፣ ማህበራት እና ትምህርት ቤቶች ምስጋና እና ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

‎ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን