የሰንበት ገበያ ማዕከል ሸማቹና አምራቹ ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የላቀ ሚና እንዳለው ተገለጸ
ሀዋሳ፡ 25/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሰንበት ገበያ ማዕከል ሸማቹ እና አምራቹ ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የላቀ ሚና እንዳለው ገልጿል፡፡
የማረቆ ልዩ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ሸማቹን ማህበረሰብ ከአምራቹ ጋር በቀጥታ ለመስተሳሰር ያስገነባውን የሰንበት ገበያ ማዕከል ስራ አስጀምሯል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ማዕከሉን አገልግሎት እንዲሰጥ መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፤ የሰንበት ገበያ ማዕከል ሸማቹ እና አምራቹ ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የላቀ ሚና አለው።
እስካሁን ባለው 104 የሰንበት ገበያዎችን ማቋቋም ስለመቻሉም ጠቁመዋል።
በልዩ ወረዳው የተቋቋመው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የሰንበት የግብይት ማዕከላት በሰንበት ብቻ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ከሰንበት እስከ ሰንበት በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
የማረቆ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አማሮ በበኩላቸው፤ የሰንበት የገበያ ማዕከሉ የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ኑሯቸውን ለማሻሻል በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎቱ ማግኘት እንዲችሉ ታስቦ በክልሉና በልዩ ወረዳው ክትትል የተገነባ መሆኑን ገልፀዋል።
አክለውም አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በቅርበት ተከታትሎ ለመቆጣጣር የሚረዳ መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው አመላክተዋል።
የማረቆ ልዩ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነይማ ቆርቻ በበኩላቸው፤ የሰንበት ገበያ ማዕከሉ አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ የሚያቀርቡበት ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝበት እንደሆነ ገልፀዋል።
ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ በፊት መደበኛውን የገበያ ቀን ብቻ ጠብቀው ይገበያዩ እንደነበር ጠቁመው አሁን ግን ሳምንቱን ሙሉ መጠቀም እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በማዕከሉ ስራ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙ የስራ ኃላፊዎች በቆሼ ከተማ ግንባታቸው እየተጠናቀቁ የሚገኙ የሁለት ማደያዎች ግንባታ ያሉበትን ደረጃ ተመልክተዋል።
ዘጋቢ፡ ዘይኔ ሁንዲቶ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ከ36 ሚሊዬን ብር በላይ ወጪ የተሰራው የኡማ ባኬ መንገድ ተጠናቆ ተመረቀ
የ2017 የክረምት ወራት የገቢ አሰባሰብና የ2018 ዓ.ም የንግድ ፈቃድ ምዝገባና እድሳት ስራ በአግባቡ ለመስራት መዘጋጀታቸውን በጋሞ ዞን ባለድርሻ አካላት ገለጹ
የክልሉ ኦዲት ግኝት አስመላሽ ኮሚቴ አበረታች ሥራ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ