የ2017 የክረምት ወራት የገቢ አሰባሰብና የ2018 ዓ.ም የንግድ ፈቃድ ምዝገባና እድሳት ስራ በአግባቡ ለመስራት መዘጋጀታቸውን በጋሞ ዞን ባለድርሻ አካላት ገለጹ
ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አኳያ የሚታዩ ውስንነቶችን በመቅረፍና ተጠያቂነትን በማስፈን በየደረጃው የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁም ተጠቅሷል።
የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ የ2017 የግብር ዘመን የግብር መክፈያ ወቅት ማስጀመሪያና የ2018 የንግድ ፈቃድ ምዝገባና እድሳት የንቅናቄ መድረክ በተካሄደበት ወቅት የውይይት መነሻ ሰነድ የቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባና በየማዕከላቱ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ የሰው ሀይል ከወዲሁ መሟላቱን ጠቅሰው ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አኳያ የሚታዩ ውስንነቶችን በመቅረፍና ተጠያቂነትን በማስፈን በየደረጃው የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
እንዲሁም ግብርን በቴሌ ብር ከማስከፈል ጋር ተያይዞ የሚታየውን ተግዳሮት ለመቅረፍ ከቴሌ ኤጀንቶች ጋር የግንዛቤ ስራዎችን ከወዲሁ በመስራት የ2017 የክረምት ወራት የገቢ አሰባሰብና የ2018 የንግድ ፈቃድ ምዝገባና እድሳት ስራ በአግባቡ ለመስራት መዘጋጀታቸውን በአስተያየታቸው ጠቅሰዋል።
የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ ወ/ሪት ሰላማዊት ቦዳ፤ የንግዱ ማህበረሰብ ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ግብሩን በሚከፍልበት ወቅት የ2018 የንግድ ፈቃድ ምዝገባና እድሳቱንም አብሮ ማስኬድ እንደሚገባውና በዚህ ረገድ እንደ ዞን በተቀመጠው አጭር ቀን ውስጥ ከ18 ሺ በላይ የንግድ ፈቃድ እድሳትና ምዝገባ እንደሚከናወን፤ 11 ሺ የሚሆኑት በቴሌ ብር አገልግሎት ክፍያቸውን እንደሚፈጽሙ ተናግረዋል።
የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ ሀላፊ አቶ ቶማስ ቶቤ በበኩላቸው፤ ሲስተም ያልተዘረጋባቸው ወረዳዎች በማንዋል የሚከፍሉ መሆኑንና የተቀሩት በተዘረጋው ሲስተም መሰረት ቴክኖሎጂ በመጠቀም መክፈል እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
ለዚህም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ቅንጅታዊ ስራ መሰራቱን የጠቀሱት አቶ ቶማስ፤ የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ግብር ጋር ተያይዞ በተቀመጠው ምጣኔና ጊዜ ገደብ ከፍሎ ማጠናቀቅ እንዲቻል የሁሉንም ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል።
የጋሞ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሀኪሜ አየለ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ፤ ከሀምሌ አንድ ጀምሮ የሚከናወነው የገቢ አሰባሰብ ንቅናቄ የተሳካ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ቅንጅት የተጠናከረ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ከወዲሁ መቅረፍ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ሀኪሜ፤ የጠራ መረጃ በመያዝና የተቀናጀ ስራ በመስራት የዞኑን የገቢ አሰባሰብ የተሳካ እንዲሆን ልንረባረብ ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ: ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የክልሉ ኦዲት ግኝት አስመላሽ ኮሚቴ አበረታች ሥራ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
የትምህርት ቤቶችን የትምህርት ግብዓት ችግር ለመቅረፍ የውስጥ ገቢ አቅምን የማሳደግ ስራ እየተሠራ እንዳለ ተገለፀ
በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሞዴል የማሕበረሰብ መድኀኒት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ