የክልሉ ኦዲት ግኝት አስመላሽ ኮሚቴ አበረታች ሥራ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የክልሉ ኦዲት ግኝት አስመላሽ ኮሚቴ የሕዝብና መንግስት ሃብት በማስመለስ አበረታች ሥራ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አስታወቀ፡፡
ግብረ ኃይሉ በ2017 ባከናወነው ሦስት ዙር ድጋፋዊ ክትትል የክልሉን አፈፃፀም ከ 6 ነጥብ 3 ወደ 70 በመቶ ማድረስ መቻሉን በሚዛን አማን ከተማ በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ ተመላክቷል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ ወንድሙ ኩርታ እንዳሉት፥ በመንግስት ሃብትና ንብረት አስተዳደር በኦዲት ግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድ የተጠያቂነት አሠራር መሻሻል አሳይቷል፡፡
ከ2014 እስከ 2016 ዓ.ም በ 47 መሥሪያ ቤቶች ላይ በተደረገ የኦዲት ሥራ ከ 19 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ ከማድረግ ባለፈ ከ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመው፥ ሥራው ቀደም ብሎ ተጀምሮ ቢሆን ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻል እንደነበር የሚያሳይ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ የተሰጣቸውን አስተያየት በመቀበል ፈጥነው የወጡ ተቋማትና መዋቅሮች የመኖራቸውን ያህል፥ አሁንም መሻሻል ያልቻሉ በመኖራቸው የተጠያቂነት አሰራርን ለማረጋገጥ ይሰራል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ልዩ አማካሪ እና የግብረ ኃይሉ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ንጉሴ ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው፥ የተገኘባቸውን የኦዲት ግኝት እስከ ዓመቱ መጨረሻ እንዲያስተካክሉ የተቀመጠውን አቅጣጫ መተግበር ባልቻሉ ላይ ህጋዊ ሥርዓትን ለማስፈን ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
በቀጣይ የእርምት እርምጃ በመወሰድ ፈጣን ለውጥ ማምጣት የቻሉ ተቋማትና መዋቅሮችን በመደገፍ ተሞክሯቸውን ለማስፋት እና ሥራቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉበት የድጋፍ ሥርዓት እንደሚዘረጋ ጠቁመው፥ የሚመለሰው የሕዝብና መንግስት ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የማረጋገጡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊ አቶ አስራት አበበ በአንፃሩ የኦዲት ሥራው ሲጀመር በታችኛው መዋቅር አካባቢ ቅሬታ አዘል ሥጋት እንደነበር አስታውሰው በተሰራው ሥራ ግን አሁን ላይ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በክልሉ የተፈጠረው መነቃቃት ለሃገር ጭምር ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው ሥራውን በማጠናከር የክልሉን ዕድገት በማፋጠን የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማስቀጠል በቅንጅት መሥራት ከባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የክልሉ ኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ ኃይል በሦስት ዙር ባደረገው የኦዲት ግኝት የእርምት እርምጃ አወሳሰድ ድጋፋዊ ክትትል፤ በመጀመሪያ ዙር የነበረውን የ 6 ነጥብ 37 በመቶ አፈፃፀም በሁለተኛው ዙር 50 ነጥብ 77 በመቶ ማድረሱን እና በሦስተኛው ዙር አፈፃፀሙን ወደ 70 በመቶ መድረሱን በመድረኩ የቀረበው ሪፖርት አመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡ ካሱ ብርሃኑ
More Stories
የትምህርት ቤቶችን የትምህርት ግብዓት ችግር ለመቅረፍ የውስጥ ገቢ አቅምን የማሳደግ ስራ እየተሠራ እንዳለ ተገለፀ
በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሞዴል የማሕበረሰብ መድኀኒት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪስቶች ምቹ ማረፊያ እንዲሆን በዙሪያው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው እያለሙ ያሉ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑሪ ከድር ገለፁ