በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሞዴል የማሕበረሰብ መድኀኒት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዋቸሞ ዩንቨርስቲ በሀዲያ ዞን ጊንቢቹ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ሞዴል የማሕበረሰብ መድኀኒት ቤት አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የመድኃኒት ቤቱ መገንባት ገንዘብ እና ጊዜ ከመቆጠብ ባለፈ እንግልትን የሚያስቀር በመሆኑ ደስታ እንደተሰማቸው አንዳንድ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።
የጊንቢቹ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታገሰ ተመስገን ዩንቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራ ጎን ለጎን ሰው ተኮር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በሆስፒታሉ አቅም ማሟላት የማይችላቸውን ግብዓቶች በማቅረብ ሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ አስችለዋል ያሉት ከንቲባው፥ በዕለቱ ለስድስት ወረዳዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ በማድረግ ተገንብቶ መድኀኒት በማሟላት ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው መድኀኒት ቤት የሕዝቡን የዘወትር ጥያቄ የመለሰ እንደሆነ አንስተዋል።
በሰለጠነ የሰው ሀይልና በህክምና ቁሳቁስ ዕጥረት ሕብረተሰቡ ወደ ሌሎች ህክምና ተቋማት በመሄድ እንዳይጉላላ ዩንቨርስቲው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕሬሄንስቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኤክስክዩቲቪ ዳይሬክተር ዶ/ር ይድነቃቸው ዳዳቸው እንደገለጹት ሆስፒታሉ ለተገልጋዮች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ በተደረገው ርብርብ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
ጤናማ ሕብረተሰብ ከሌለ ልማት እንደማይታሰብ የተገነዘበው ሆስፒታሉ የውስጥ አገልግሎት አሰጣጡ የሕብረተሰብ ተጠቃሚነቱን የበለጠ እንዲያረጋግጥ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ከመፈጸም ባለፈ በሀዲያ ዞን ያሉትን አራት ሆስፒታሎች በሰው ሀይል፣ በግብዓት አቅርቦት እና በቴክኖሎጂ እየደገፈ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ይድነቃቸው፥ መድኀኒት ቤቱ ለሕብረተሰቡ ዘላቂነት ያለውን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል የሽያጩ ገንዘብ ሳይባክን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
ሞዴል የማሕበረሰብ መድኀኒት ቤቱ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ዶክተር ይድነቃቸው ጠቅሰዋል::
የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ መድኀኒት ቤቱን መርቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፥ ተቋሙ ለአከባቢው ማህበረሰብ ዘርፈ-ብዙ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።
መሰል የልማት ተግባራቱ በሁለም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፥ ባለድርሻ አካላት የተሰሩ ስራዎች እንዳይበላሹ መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል ።
በምረቃ ፕሮግራሙ አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው የመድኃኒት ቤቱ መገንባት ገንዘብ እና ጊዜ ከመቆጠብ ባለፈ እንግልትን የሚያስቀር ስለሆነ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ወቅት የጊንቢቹ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን የጎበኙ ሲሆን ከግብዓት አቅርቦት አንጻር የተነሱ ጥያቄዎችን ባጠረ ጊዜ ለመመለስ እንደሚሰራ ቃል ተገብቷል።
ዘጋቢ: ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪስቶች ምቹ ማረፊያ እንዲሆን በዙሪያው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው እያለሙ ያሉ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑሪ ከድር ገለፁ
እራሱን ወደ ኢንተርፕራይዝ ከፍ በማድረግ በሃገር ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚፈልግ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በጂንካ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጎዳና የወጡ ህጻናትን ሥራ ዕድል እንዲያገኙ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው