የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪስቶች ምቹ ማረፊያ እንዲሆን በዙሪያው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው እያለሙ ያሉ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑሪ ከድር ገለፁ

የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪስቶች ምቹ ማረፊያ እንዲሆን በዙሪያው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው እያለሙ ያሉ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑሪ ከድር ገለፁ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ከባለድርሻ ጋር የሚደረግ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን የሚገኝ ሲሆን በውስጡ ከ150 በላይ ለመድኅኒትነት የሚውሉ የዛፍ ዝርያዎች፣ የተለያዩ ብርቅዬ አእዋፋት እንዱሁም የዱር እንስሳት መገኛ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑሪ ከድር፤ ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በክልሉ ብቸኛው በመሆኑ ክልሉ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ የፓርኩን እምቅ አቅም ለመጠቀም በርካታ ስራ እየተሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ባለፋት አመታት ፓርኩ ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል ያሉት አቶ ኑሪ፤ በውስጡ ያለ እምቅ አቅም ለመጠቀም በተሰራው ስራ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ማረፊያ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።

ብሔራዊ ፓርኩን ይበልጥ ለማልማት በዙሪያው በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ያለመ ምክክር መድረክ መሆኑንም አቶ ኑሪ ተናግረዋል።

የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ተካ በበኩላቸው፤ ፓርኩ የአካባቢውን ብዝሃ ሕይወት በመጠበቅ እና የተፈጥሮ ሀብቱን ጠብቆ በዘላቂነት ለማቆየት ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

እንደ አቶ መሰፍን ገለፃ፤ የብሔራዊ ፓርኩ ስነ ምህዳር መጠበቅ የግቤ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኅይል ማመንጫ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።

ፓርኩን በአግባቡ ማልማት ከተቻለ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶቾን በመሳብ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ትልቅ አቅም አለው ያሉት አቶ መስፍን፤ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር የስራ ዕድል የሚፈጥር ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ አመተሩፍ ሁሴን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሀላፊዎች፣ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ እና ባለሀብቶች በፓርኩ ዙሪያ ያሉ የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ተዘራ በቀለ – ከወልቂጤ ጣቢያችን