ዳራማሎ ደንዳሾ ስፖርት ክለብ ባስኬት ቡናን  በማሸነፍ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና የዋንጫ አሸናፊ ሆነ

ዳራማሎ ደንዳሾ ስፖርት ክለብ ባስኬት ቡናን  በማሸነፍ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና የዋንጫ አሸናፊ ሆነ

20 ክለቦችን በማሳተፍ ለሦስት ሳምንት ሲካሄድ  የነበረው 2ኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ተጠናቋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ በንግግራቸው ክልሉ በስፖርቱ ዘረፍ ትልቅ አቅም እንዳለው ያየንበትና ብሎም ስፖርቱ ለህዝብ አንድነትና አብሮነት ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በመረዳት ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መንገድ በመካሄዱ መላውን ህዝብ አመስግነዋል።

በቀጣይም ሀገር አቀፉ የእግርኳስ ውድድር ከሰኔ 28/2017 ጀምሮ ለአንድ ወር በጂንካ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን ለዚሁም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው ስፖርቱ ሠላምን በማፅናት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረውና ዞኑም ስኬታማ የሆነ ክልል አቀፍ ውድድር ማካሄዱን ገልፀው በቀጣይ በሀገር አቀፉም ይህንኑ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደረሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወ/ሚካኤል መስቀሌ የዚህ ውድድር ዋና አላማ በክልል ደረጃ የክልሉን አንድነት በማጠናከር፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና በየዞኑ ያለውን የእግርኳስ እንቅስቃሴ ለመመዘን ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ውድድሩ ቡርጂ ዞን ብቻ ሲቀር 11ዱ ዞኖች የተሳተፉበት ሲሆን በዚህም ከአንድ እሰከ አራት የወጡ ክለቦች ማለትም ዳራማሎ ደንዳሾ፣ ባስኬት ቡና፣ ኛንጋቶምና ኮንሶ ኒውዮርክ በሀገር አቀፉ ውድድር ክልሉን የሚወክሉ ይሆናል ብለዋል።

የኣሪ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ይኸነው ተስፋዬ እንደ አዘጋጅ ከተማ ውድድሩ ስኬታማ እንደነበር ገልፀው የህዝቡን አንድነት በማጠናከር እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ከ6 መቶ በላይ የዞኑን ወጣት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ለዋንጫ በተደረገው ጨዋታ ዳራማሎ ደንዳሾ ስፖርት ክለብ ባስኬት ቡናን  2ለ1 በማሸነፍ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።

በተመሳሳይ ከዋንጫ ጨዋታው አስቀድሞ ኛንጋቶም ወረዳን ከኮንሶ ኒውዮርክ ያገናኘው የደረጃ ጨዋታ ሙሉ ደቂቃ ሁለት አቻ በመለያየታቸው በመለያ ምት ኛንጋቶም  ወረዳ 5ለ3 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃ በማግኘት የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

የየክለቡ ተጫዋቾችም ጠንካራ ቡድን መስርተን ሀገር አቀፉ ውድድር ክልሉን ወክለው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን