“በማንቸስተር ዩናይትድ ልዩ ነገር መስራት እንደምንችል ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ” – ማይክል ካሪክ

“በማንቸስተር ዩናይትድ ልዩ ነገር መስራት እንደምንችል ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ” – ማይክል ካሪክ

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ከአዲሱ የውድድር ዘመን መጀመር አስቀድሞ በሰጠው አስተያየት፣ ቡድኑ ትልቅ ስኬት የማስመዝገብ አቅም እንዳለው ገልጿል።

ቀያዮቹ ሰይጣኖች ከአዲሱ የውድድር ዘመን ዝግጅት መጠናቀቅ እና ከዝውውር መስኮቱ መዘጋት በፊት ስብስባቸዉን ለማጠናከር እየሰሩ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ ካሪክ አሁንም ተጨማሪ የዝውውር ፍላጎቶች እንዳሉት ይፋ አድርጓል።

ማይክል ካሪክ በሰጠዉ አስተያየት “ያለንን ስብስብ ስትመለከቱ በጥሩ ሚዛን ላይ ይገኛል፤ ነገር ግን አሁንም ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን እንፈልጋለን” ብሏል፡፡

አሰልጣኙ አክሎም “ቡድኑ ከዚህ በላይ እንዲሆን እንፈልጋለን፤ ቡድናችንን ወደፊት ለመግፋት ጥረታችንን መቀጠል አለብን። ማሻሻል የምንፈልጋቸው አንድ ወይም ሁለት ቦታዎች አሉ” ሲል ተናግሯል፡፡

ማንቸስተር ዩናይትድ በዝውውር መስኮቱ እንደ አንድሪ ሳንቶስ እና ዩሪ ቴሌማንስ ያሉ አማካዮችን ወደ ስብስቡ የቀላቀለ ቢሆንም፣ ካሪክ የቡድኑን ጥራት እና ጥልቀት ለመጨመር በተለይም በግራ መስመር ተከላካይ እና አማካይ ስፍራዎች ላይ ተጨማሪ ተጫዋቾችን የማስፈረም ፍላጎት እንዳለው አመልክቷል።

ዩናይትድ በካሪክ እየተመራ ያለፈውን የውድድር ዘመን በ3ኛ ደረጃ በማጠናቀቅ ወደ ቻምፒየንስ ሊግ መመለሱ ይታወቃል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ