ማርከስ ራሽፎርድ እና እሱን ያገለለው አሰልጣኝ ዳግም ግጥምጥሞሽ

ማርከስ ራሽፎርድ እና እሱን ያገለለው አሰልጣኝ ዳግም ግጥምጥሞሽ

እግር ኳስ ሁልጊዜም አስገራሚና ያልተጠበቁ አጋጣሚዎችን በማስተናገድ ይታወቃል።

በዛሬው ዕለት በፖላንድ ሮክላው ከተማ በሚካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ከፍተኛ ተከፋዩ አጥቂያቸው ማርከስ ራሽፎርድ እና የቀድሞ አሰልጣኛቸው ሩበን አሞሪም የሚያገናኝ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ሊጻፍ ተዘጋጅቷል።

ባለፈው የውድድር ዘመን መጀመሪያ ላይ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በማንቸስተር ዩናይትድ በነበራቸው ቆይታ ራሽፎርድን ከዋናው ቡድን ለይተው «ቦምብ ስኳድ» በመባል ከሚታወቀው ገለልተኛ የልምምድ ስብስብ ጋር እንዲሰለጥን አስገድደውት ነበር።

ይህንንም ተከተሎ ተጫዋቹ ሙሉ የውድድር ዘመኑን በውሰት በባርሴሎና ለማሳለፍ ተገዷል። በወቅቱ የነበረው ሁኔታ የ28 ዓመቱ እንግሊዛዊ አጥቂ በዩናይትድ ቤት ያለው ቆይታ ፈጽሞ ያበቃ የሚመስል ነበር፤ ቡድኑም ይለብስ የነበረውን 10 ቁጥር ማሊያ ለአዲሱ ፈራሚ ማቴዎስ ኩኛ አሳልፎ መስጠቱ ይህንን ግምት አጠናክሮት ነበር።

ነገር ግን ከ12 ወራት በኋላ የሁኔታዎች መለዋወጥ ማንንም የሚያስገርም ሆኗል።

ዛሬ ላይ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ማንቸስተር ዩናይትድን ለቀው የጣሊያኑን ክለብ ኤሲ ሚላንን በዋና አሰልጣኝነት ተረክበዋል።

በአንጻሩ በብዙዎች ዘንድ “የኦልድትራፎርድ ቆይታው አብቅቶለታል” የተባለው ማርከስ ራሽፎርድ፣ በአዲሱ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ የሚመራውን የልጅነት ክለቡን ማሊያ ዳግም ለብሶ ለመጫወት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

የበለጠ ትኩረት ሳቢ የሚያደርገው ደግሞ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ አዲሱን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዘመን ነሐሴ 16 ቀን ከአዲስ አዳጊው ሀል ሲቲ ጋር በመጫወት ከመጀመሩ በፊት የሚያደርገው የመጨረሻ ቅድመ-ውድድር ዘመን ወዳጅነት ጨዋታ ከዚሁ የሩበን አሞሪሙ ኤሲ ሚላን ጋር መሆኑ ነው።

የሁለቱ አካላት ዳግም መገናኘት ለወዳጅነት ጨዋታው የተለየ የውጥረት እና የስሜት ግለት የሚሰጥ ሲሆን፣ ራሽፎርድ በዩናይትድ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ላለው ፍላጎት ትልቅ ማረጋገጫ እንደሚሆን ይገመታል።

ይህ የወዳጅነት ጨዋታ ዛሬ አመሻሽ 11 ሰዓት ከ45 ላይ ይደረጋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ