እራሱን ወደ ኢንተርፕራይዝ ከፍ በማድረግ በሃገር ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚፈልግ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ
የከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ሽፋን ከ93 በመቶ በላይ መደረሱም ተጠቁሟል።
የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ አማን ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወልቂጤ ጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ድርጅቱ በበጀትና በግብአት አደራጅቶ በራሱ መተዳደር እንዲችል የደረጃ አንድ የውሃ ኮንስትራክሽን ስራዎች ፍቃድ በማውጣት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየሰራ ይገኛል።
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የውሃና የመስኖ ፕሮጀክቶችን በውላቸው መሰረት በጥራትና በፍጥነት እየገነባ በውጤታማነት በማስረከብ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ሰይድ፤ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመሆኑም ድርጅቱ እራሱን ወደ ኢንተርፕራይዝ በማሳደግ በሃገር ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አቶ ሰይድ አስገንዝበዋል።
በሌላ መልኩ በውሃ ማማ ላይ እንደተቀመጠች የሚነገርላት ቡታጅራ ተጠቃሚው ህብረተሰብ የ24 ሰአት የውሃ አገልግሎት በቀጥታ እንደሚያገኝ የተናገሩት ስራ አስኪያጁ፤ አሁን ላይ የከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ሽፋን ከ93 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት በከተማው በሰከንድ 105 ሊትር ውሃ ማምረት የሚችሉ 6 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች እንዳሉ በመግለጽ በየጊዜው የከተማው ስፋትና የህዝብ ቀጥር መጨመርን ታሳቢ በማድረግ የተጠኑ ሌሎች ሶስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች መኖራቸውንና በየአመቱም አንዱን በመቆፈር አገልግሎት ላይ እንዲውል የቅድሚያ አቅድ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ ድርጅቱ በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ ብሎም በበጀት እራሱን በማደራጀት ህብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ የንጹህ መጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ከማድረግ ባሻገር የፍሳሽ አገልግሎት መስጠት እንዲችል በጣሊያን መንግስት በተገኘ 5 መቶ 44 ሚሊየን ብር ድጋፍ የሳኒቴሽን ፕሮጀክት ለመገንባት ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር ተገብቷል።
ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሞዴል የማሕበረሰብ መድኀኒት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪስቶች ምቹ ማረፊያ እንዲሆን በዙሪያው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው እያለሙ ያሉ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑሪ ከድር ገለፁ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በጂንካ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጎዳና የወጡ ህጻናትን ሥራ ዕድል እንዲያገኙ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው