የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በጂንካ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጎዳና የወጡ ህጻናትን ሥራ ዕድል እንዲያገኙ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው
በዛሬው ዕለት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በሊስትሮ ጫማ መጥረግ ሥራ ገቢ የሚያገኙበትን ሼድ በማስገንባትና የመስሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከጂንካ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ለጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትና ለሌሎችም ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል እንዲመቻች በትብብር እየሰራ ይገኛል።
በድጋፍ መርሐ ግብሩ የተገኙት የጂንካ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ግርማ ገብረ፤ ዩኒቨርሲቲው በከተማው ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ ላለው ተግባር አመስግነው ሥራ ዕድል የተመቻቸላቸው ህጻናትም ዕድሉን በመጠቀም ለተሻለ ህይወት በትጋት እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ አስተባባሪና መምህር አያሌው ስመኝ የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተለያዩ ዘርፎች ዘላቂ ሥራ ዕድል እንዲያገኙ እና ከአደንዛዥ ዕጽና ከጎዳና ተዳዳሪነት እንዲወጡ ለማስቻል ዩኒቨርስቲው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አእምሯዊና ማህበራዊ ደህንነትን ለመጠበቅና በጎዳና ተዳዳሪዎች ህይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ያሉት የጂንካ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ የአለም ግርማ፤ 2 መቶ ለሚጠጉ ጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት በዘላቂነት ሥራ ዕድል እየተመቻቸላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ኃላፊዋም አክለውም ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረገው ትብብር ከዚህ ቀደም ለ20 ህጻናት በዛሬው ዕለት ደግሞ ለ10 ልጆች በሊስትሮ ጫማ መጥረግ፣ በእጅ ጋሪና በሌሎችም ሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ተደርጓል ብለዋል።
ሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ህፃናትም በተሰጠው ሥራ ዕድል መደሰታቸውን ጠቁመው በቀጣይ ኑሯቸውን ለመሻሻልና ለተሻለ ህይወት በትጋት እንሰራለን ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሞዴል የማሕበረሰብ መድኀኒት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪስቶች ምቹ ማረፊያ እንዲሆን በዙሪያው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው እያለሙ ያሉ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑሪ ከድር ገለፁ
እራሱን ወደ ኢንተርፕራይዝ ከፍ በማድረግ በሃገር ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚፈልግ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ