የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ ድጋፍ ከ2.6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በከምባታ ዞን ለሀምቦ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
በድጋፍ ፕሮግራሙ ላይ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶን ጨምሮ የተለያዩ የዩንቨርሲቲው ማህበረሰብ አካላት ተገኝተዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ በድጋፍ መርሃ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በሚያከናውናቸው ስራዎች ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በከምባታ ዞን ለሀምቦ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ2.6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የማይክሮስኮፕ፣ ኮምፒውተር እና መሰል ለትምህርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በሀዲያና ከምባታ ዞኖች ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ተግባራትን በማከናወን ህብረተሰቡን እያገለገለ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ሎለሞ ናቸው።
ከዞን እና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ በመሆን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ እንሰራለን ያሉት ዶ/ር አበበ፤ ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት ቤቶችን የማሻሻል ፕሮግራምን ለ3 አመታት አቅዶ እየሰራ እንደሆነም አክለዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የዱራሜ ካምፖስ ቺፍ ኤክስኪውቲቨ ዳይሬክተር አቶ ዘውዴ ክፍሌ በበኩላቸው፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትልቅ ንቅናቄ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የትምህርት ፖሊሲዎችን በማሻሻል፣ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ የተሻሻሉ ትምህርት ቤቶችን ለዜጎች ለመገንባት ዩኒቨርስቲው ከመንግስት ጋር በመሆን በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሴ ዳንኤል፤ በቀጣይ 3 አመታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
የዛሬው የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍም የዚሁ ማሳያ እንደሆነም አንስተዋል።
በመጨረሻም ከዩኒቨርሲቲው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የሀምቦ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ረዳልኝ አንቆሬ፤ በቀጣይም የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የሚረዱ በርካታ ስራዎችን ከዩኒቨርስቲው ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በድጋፍ ፕሮግራሙም ላይ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት አካላትን ጨምሮ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ እና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ኤደን ተረፈ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በጎፋ ዞን ከ950 ቶን በላይ የብረት ማዕድን ክምችት መኖሩ ተገለጸ
በክልሉ የሚከናውኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሊሆኑ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ገለፁ
የአፈርና ውሃ ጥበቃ በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ