የፌደራል ስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም በቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ቤንች ወረዳ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የድልድይ ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ ገለፀ

የፌደራል ስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም በቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ቤንች ወረዳ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የድልድይ ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ ገለፀ

የድልድይ ግንባታው ሲጠናቀቅ አርሶ አደሩ ምርታቸውን በቀላሉ ለገበያ በማቅርብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋገጡ እንደሚያግዛቸውም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገረዋል።

የደቡብ ቤንች ወረዳ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን የሚያስገኙ የቅመማ ቅመም ምርትን ጨምሮ ቡና፣ ሙዝ፣ በቆሎ፣ ሽንኩርትና የተለያዩ ምርቶችን በስፋት የሚያመርት አካባቢ በመሆኑ ማህበረሰቡን የሚያግዝ መንገድና ድልድዮችን በህብረተሰብ ተሳትፎ እየገነባ ይገኛል።

ተሳትፎውን ለማጠናከር በወረዳው 4 ቀበሌያትን ጃንቹታ፣ ሞሪታ፣ ጃንቹና ዲሪታን የሚያገናኘው የዛን ወንዝ ድልድይ ግንባታ በፌደራል ስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም እየተገነባ በመሆኑ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ የወረዳው ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ለገሰ ገልፀው፤ የድልድዩ መገንባት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ያሳልጣል ብለዋል።

የህብረተሰቡን የመንገድና የድልድይ መሠረተ ልማት ችግሮችን የተረዳው የፌደራል ስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ዕጥረቱን ለመቅርፍ በ20 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በጀት ድልድይ እያስገነባ እንደሚገኝ በወረዳው በግብርናና አካባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ ጽ/ቤት የስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ካፒቶ ተናግረዋል።

የድልድይ ግንባታው እንዲፋጠን ክልሉ ለወረዳው የስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ውክልና ሰጥተው የድጋፍና የክትትል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝና አፈፃፀሙ ከ90 በመቶ በላይ መድረሱን አስተባባሪው አውስተው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ምርቱን በቀላሉ ወደ ገቢያ በማውጣት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ብለዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ወርቅነሽ ሜሩኮይ እና አቶ ማቴዎስ ተሾመ በበኩላቸው፤ በክረምት ወንዝ ሲሞላ ደረጃውን የጠበቀ ድልድይ ባለመኖሩ ምርታቸውን ለገበያ ለማውጣትና ወደ ህክምና ቶሎ ለመድረስ በትራንስፖርትም እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም በአካባቢያቸው ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ምርቶችን ቢያመረቱም በመንገድና ድልድይ አለመኖር ንብረታቸው እየባከነ እንደሆነ ገልፀው፤ አሁን በመገንባት ላይ ያለው ድልድይ ከተጠናቀቀ የተሻለ ተስፋ እንዲኖራቸው ማደረጉን አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን