ከ54 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በክልሉ የሶላር ፓምፖች ተከላ እየተከናወነ እንደሚገኝ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ገለፀ
ኤጀንሲው በቀቤና ልዩ ወረዳ ቄረምሳ ቀበሌ የፕሮጀክት አፈፃፀም የመስክ ምልከታ አድርጓል።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ካሳዬ ተክሌ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ክልሉ በአዲስ መልክ ከተደራጀ ወዲህ ኤጀንሲው ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ ይገኛል።
በክልሉ በሃላባ ዞን፣ በቀቤና እና ማረቆ ልዩ ወረዳዎች የ70 ሶላር ፓምፖች ገጠማ ሥራ ከ54 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ስራው ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ጥናት በማድረግ ሶላር ፓምፖቹ አመቱን በሙሉ የውሃ አቅም እንዳላቸው ከተረጋገጠ በሗላ እንደሆነ ኢ/ንጂነር ካሳዬ ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል በቀቤና ልዩ ወረዳ በተመረጡ ቀበሌዎች 30 የሶላር ፓምፖች ገጠማ እንደሚከናወን አንስተዋል።
ውሃን በማከም ከመስኖ ውሃነት በተጨማሪ ለመጠጥነት እንደሚያገለግልና እነዚህ የተጀመሩ ስራዎች ግምገማ ከተከናወነ በሗላ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚስፋፋ ገልጸዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በበኩላቸው የቀቤና ልዩ ወረዳ ለመስኖ ስራ አመቺ፣ በሁለት ትላልቅ ወንዞች መሐል የሚገኝና የከርሰ ምድር ውሐ በቅርበት የሚገኝበት ወረዳ መሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉ መስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳር ኤጀንሲ በልዩ ወረዳው እያከናወነ የሚገኘው የሶላር ፓምፖች ግንባታ ትልቅ እድል መሆኑን በመጥቀስ፤ ማህበረሰቡ መዘናጋት ሳይኖር በጥንቃቄ በመጠቀም ምርትና ምርታማነት እንዲያሳድግ አቶ ሞሳ መልእክታቸው አስተላልፈዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አቡበክር ዱላ፤ የብልፅግና ፓርቲ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
አቶ አቡበከር አክለውም አርሶ አደሩ የራሱንና የቤተሰቡን ጉልበት ተጠቅሞ የምግብ ዋስትናው ከማረጋገጥ ባሻገር ሃብት ለማፍራት ከምንጊዜውም በላይ ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ውሃ ማእድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ከድር ደገፋ፤ የክልሉ መንግስት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚሰራቸው ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አርሶ አደሩን በማህበር በማደራጀት በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አንድ የመስኖ ፓምፕ ጉድጓድ ከስድስት እስከ ሰባት አርሶ አደር በኩታ ገጠም የሚያለማበትና ከእኔነት አስተሳሰብ በመውጣት በጋራ የመስራትና የማደግ ተምሳሌት ነው ብለዋል።
አቶ ከድር አክለውም፤ በአንድ የመስኖ ጉድጓድ ስድስት ሔክታር መሬት እንደሚለማ ገልፀው በአመት ሶስት ጊዜ በማልማት 18 ሔክታር መሬት የማልማት እድል ያለው ፕሮጀክት መሆኑን አመላክተዋል።
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አርሶ አደር የሆኑት አቶ ሚፍታ ግራኝ፣ ሰኢድ እና ሞሳ ሙባረክ በሰጡን አስተያየት፤ የመስኖ ልማት ቀደም ብለው እንደጀመሩ ገልፀው መንግሰት ይህንን ስራ በመስራቱ ከራሳቸው የቤት ፍጆታ አልፎ ለገበያ ምርት እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
ይህም በአመት ሁለት ጊዜና ከዛ በላይ ለማምረት እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ፍስሃ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የክልሉ ኦዲት ግኝት አስመላሽ ኮሚቴ አበረታች ሥራ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
የትምህርት ቤቶችን የትምህርት ግብዓት ችግር ለመቅረፍ የውስጥ ገቢ አቅምን የማሳደግ ስራ እየተሠራ እንዳለ ተገለፀ
በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሞዴል የማሕበረሰብ መድኀኒት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ