በዞኑ በቦረዳ ወረዳ የ2017 ምርት ዘመን በልግ ወቅት እየለማ የሚገኝ የበቆሎ ክላስተር ማሳ ጉብኝት ተካሂዷል።
በጉብኝቱ ወቅት የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ደምሴ አድማሱ እንደገለፁት፤ ዞኑ በግብርና ዘርፍ ዕምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች ናቸው።
በተለይም በኩታ ገጠም እርሻ በክላስተር ማልማት አርሶ አደሩን በተገቢው ለመደገፍ ምቹ ከመሆኑም ባሻገር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የጎላ አሰተዋጽኦ መኖሩን ዋና አስተዳዳሪው አሰረድተዋል።
በመሆኑም አርሶ አደሩ በዘርፉ የሚገጥመውን ችግር በመፍታት ምርቱን ለገበያ ማቅረብ እንዲችል የገበያ ትስስርና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ዞኑ አበክሮ እንደሚሰራ ዶ/ር ደምሴ አረጋግጠዋል።
የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማጌሶ ማሾሌ በበኩላቸው፤ በዞኑ ከ1 መቶ 23 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ እርሻ እየለማ መሆኑን ተናግረው፤ ከዚህም በቆሎ፣ ድንችና ቦሎቄ በ107 ቀበሌያት ከ500 በላይ በክላስተር እየለማ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም በበቆሎ ክላስተር 22 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በቦረዳ ወረዳም የበቆሎ ምርት በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ በመደረጉ የተሻለ ለውጥ መመዝገብ መቻሉን የቦረዳ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማቲዮሰ ፈለቀ ተናግረዋል።
በዚህም በወረዳው 451 ሄክታር መሬት በቆሎ እየለማ ሲሆን 3 ሺህ 500 ሄክታር በበቆሎ ክላስተር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በወረዳው የማኑካ ቀበሌ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት በቆሎን ጨምሮ የተለያዩ የሰብል አይነቶችን በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣቸውን ተናግረው፤ የመንገድና ገበያ ትስስር ችግር እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: ዓለሚቱ አረጋ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶ፣ የዕጩ ማስተዋወቂያ እንዲሁም የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራም በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ አካሄደ
ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የአይን ህክምና በሀገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
ብልጽግና ፓርቲ የማህበረሰቡ ችግር የሚቀርፉ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ በውጤታማነት ለአገልግሎት እያበቃ ነው – ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ