“በVAR ላይ እምነት የለኝም!” – ፔፕ ጋርዲዮላ
የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የዘንድሮውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት በቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR) ላይ ሳይሆን በራሳቸው ተጫዋቾች ብቃት ላይ ብቻ እንደሚተማመኑ ተናገሩ።
አርሰናል በሳምንቱ መጨረሻ በዌስትሃም ላይ ባገኘው አወዛጋቢ የVAR ውሳኔ የታገዘ ድል የነጥብ ልዩነቱን ወደ አምስት ካሰፋ በኋላ፣ ጋርዲዮላ በስርዓቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ አሰምተዋል።
“VAR ወደ እግር ኳሱ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን አምኜው አላውቅም፤ የሳንቲም ዕጣ እንደመጣል ነው” ሲሉ ጋርዲዮላ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ሲቲ ባለፉት ሁለት ተከታታይ የኤፍኤ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታዎች ላይ በVAR ውሳኔዎች ተበድሎ ዋንጫ ማጣቱን ጋርዲዮላ አስታውሰዋል።
በተለይም በ2024 ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በተደረገው ጨዋታ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በኤርሊንግ ሃላንድ ላይ የሰራው ጥፋትና ባለፈው ዓመት የክሪስታል ፓላሱ ግብ ጠባቂ ዲን ሄንደርሰን ከሳጥን ውጭ ኳስ በእጅ ነክቶ ሳይሰረዝ መቅረቱ አሁንም ድረስ አልተረሳቸውም።
“እኛ ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር ራሳችንን ማሻሻል ብቻ ነው። በዳኞች ወይም በVAR ላይ ማማረር ትኩረትን ይበትናል” ሲሉ ለተጫዋቾቻቸው መመሪያ አስተላልፈዋል።
አርሰናል ዌስትሃምን 1ለዐ ሲያሸንፍ፣ ካለም ዊልሰን በመጨረሻው ደቂቃ ያስቆጠረው ግብ በVAR ውሳኔ መሰረዙ መድፈኞቹን ለዋንጫው በእጅጉ አቅርቧቸዋል።
ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ ምሽት በኢቲሃድ ስታዲየም ክሪስታል ፓላስን ካላሸነፈ፣ አርሰናል ዋንጫውን ለማንሳት የአንድ ጨዋታ ድል ብቻ ነው የሚቀረው።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አስፈረመ
ማንቸስተር ዩናይትድ አንድሬ ሳንቶስን አስፈረመ
የ2018 የCBE የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በማሸነፍ ሁለት ዋንጫ ላነሳው የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ክልሉ ያዘጋጀውን የዕውቅናና የሽልማት ፕሮግራም ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 06/2018 ከቀኑ 12፡00 ጀምሮ በሀዋሳ ሀይሌ ሪዞርት ይካሄዳል።