የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጤናው ዘርፍ የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚድዋይፍ ማህበር ገለጸ።
ዓለም ዐቀፍ የሚድ ዋይፍ ቀን “ሚድዋይፍ- ለጤናማ ትውልድ፣ ለጠንካራ ማህበረሰብ” በሚል መሪ ቃል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በቡታጅራ ከተማ ተከብሯል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሚድዋይፍ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ተከተል ተስፋዬ የሚድዋይፍ ሙያ በእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ያመጣ መሆኑን አመላክተዋል።
በጤናው ዘርፍ የእናቶችንና ህፃናትን ጤና መጠበቅ ቅንጅታዊ ስራ የሚሻ መሆኑን የገለፁት አቶ ተከተል የበዓሉ መከበር በባለድርሻ አካላት ዘንድ የእናቶችን ጤና በአግባቡ በመጠበቅ “አንድም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም”የሚለውን መርህ ለማጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ጃማሂካ አንቻለው እንደገለፁት በበዓሉ አከባበር ወቅት እንደገለፁት የእናቶች የወሊድ ወቅት ጤና በዘርፉ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው።
ሚድዋይፍ ለሴቶችና ለጨቅላ ህፃናት ጤና ቀዳሚ የህይወት ዋስትና ነው ያሉት ዶ/ር ጃማሂካ የእናቶችንና የህፃናትን ህይወት ለመታደግ፣ በየቀኑ በሚደረጉ ጥረቶች ዘርፈ ብዙ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በ2026 የጤና ዘመን የሚድዋይፍ ሚና ከምን ጊዜውም በላይ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ማህበሩ የጤና ስርዓታችን የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ ይልቁንም የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ጤና ለመጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።
በመርኃግብሩ ላይ የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሚድዋይፍ ማህበር የፌደራል ቦርድ አባል አቶ ጀማል ኸይሩ በበኩላቸው የሚድዋይፍ ስራ ምንም እንኳ በባህሪው ከባድ ቢሆንም የዘርፉ ባለሙያዎች በሰጡት ልዩ ትኩረት በዘርፉ በሚታዩ ተጨባጭ ለውጦች አበረታች መሆናቸውን አመላክተዋል ።
በበዓሉ አከባበር ወቅትም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሚድዋይፍ ማህበር ባለድርሻ አካላት፣ በፌደራል ሚድዋይፍ ማህበር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪዎች ፣የቡታጅራ ሆስፒታል ፅንስና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስቶች፣ ዶክተሮች፣ ሚድዋይፎች፣ ነርሶችና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል ።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ ግንኙነትና አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑ ተገለጸ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸዉ – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ
የሕዝባችንን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ የመመለስና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ቁርጠኝነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)