ሀዋሳ፡ ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሴቶች የልማት ህብረትን በማጠናከር የሴቶችን ተጠቃሚነት በይበልጥ ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ “የሴቶች የልማት ህብረቶች ለክልላችን ኢኒሼቲቮች ያላቸው ሚና የጎላ ነው” በሚል መሪ ቃል ክልላዊ የሴቶች የልማት ህብረት የስትሪንግ ኮሚቴ የንቅናቄና የውይይት መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እያከናወነ ይገኛል።
የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ በመድረኩ እንደገለጹት በክልሉ በሴቶች ልማት ህብረቶች በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንና 38 ሺ 262 የሴቶች ልማት ህብረቶች፣ 124 ሺ 307 የአንድ ለአስር ትስስርና 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሴቶች ልማት ህብረት አባላት ተደራጅተው የተሻለ ተሳትፎና እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።
እንደ ክልል ለሴቶች ልማት ህብረቶች በተሰጠው ትኩረት በቁጠባ፣ በጓሮ አታክልትና ፍራፍሬ፣ በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ እንዲሁም ከግብርና ውጭ በሆኑ የስራ መስኮች በመሠማራት አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው ብለዋል።
እንደዚሁም በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች በመሠማራት ውጤታማ ከመሆን ባለፈ የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግና ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ውጤቶች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ለተቀናጀ ተግባር ተኮር ትምህርት ትኩረት በመስጠቱ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ በየደረጃው እያደገ መምጣቱን ገልጸው፥ መከላከልንና አክሞ ማዳንን መሠረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ በመተግበር ረገድም ጤናማና አምራች እንስቶች እንዲፈጠሩ እድል ፈጥሯል ብለዋል ወ/ሮ ካሰች።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ባስተላለፉት መልእክት በክልሉ ከልማትና ከተጠቃሚነት አኳያ የሴቶች የልማት ህብረትን በማሳደግ ፍትሀዊና ቀጣይነት ያለው ተጠቃሚነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የስኬት ማማ ላይ ለመድረስ ለሴቶች ተሳትፎና ውሳኔ ሰጭነት ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በሌማት ትሩፋት፣ በገቢ ማስገኛ ዘርፎች ላይ መሳተፍና የስራ እድል በመፍጠር ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሴቶችን የልማት ህብረት ማጠናከር አይነተኛ መሳርያ ነው ብለዋል።
የመከነና የባከነ ጉልበትን በማስተባበር ከሰራን ከተደጋገፍንና ከተባበርን ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልጸው ጠባቂነት ሳይኖር ከተረጅነት ለመላቀቅ ማምረትና መስራት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።
የልማት ህብረቱን በማጠናከር አምራች ባለሀብት ሴቶችን ከህብረቱ ጋር አቀናጅቶ በማስኬድ ገበያን ከማረጋጋትና የኑሮ ውድነት ጫናን ከመቀነስ አኳያ ሰፊ ስራ መስራት ይቀረናል ብለዋል አቶ ጥላሁን።
ተበድረውና ቆጥበው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሴቶችን በመደገፍና ማብቃት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከመስራት ባሻገር በሴቶች ልማት ህብረቱ ሴቶች ለውሳኔ ሰጭነት እንዲበቁ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል