የአርሰናል የድል ጉዞ እና የዌስትሃም ቁጭት!

የአርሰናል የድል ጉዞ እና የዌስትሃም ቁጭት!

የዘንድሮው የኢንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የፍጻሜ ምዕራፍ በሜዳ ላይ ድራማዎች ብቻ ሳይሆን በዳኞች ውሳኔም እየታጀበ ቀጥሏል።

ባለፈው እሁድ አርሰናል ዌስትሃምን 1 ለ 0 በረታበት ጨዋታ፣ በመጨረሻዋ ደቂቃ የተሻረው የዌስትሃም ግብ አሁንም መነጋገሪያነቱ አላበቃም።

የፕሮፌሽናል ጨዋታ ዳኞች ማህበር አለቃው ሀዋርድ ዌብ የቪኤአር (VAR) ድምጾችን ይፋ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አርሰናል በሌአንድሮ ትሮሳርድ ግብ 1 ለ 0 እየመራ ባለበት 95ኛው ደቂቃ ላይ፣ ካለም ዊልሰን የዌስትሃምን አቻ ግብ ያስቆጠረ መሰለ።

ሆኖም የቪኤአር ዳኛው ዳረን ኢንግላንድ ዋናውን ዳኛ ክሪስ ካቫናን ወደ ስክሪኑ እንዲመጣ በጠቆመው መሰረት፣ ግቡ “በግልጽ ጥፋት” በሚል ተሽሯል።

በየሳምንቱ አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎችን በሚተነትነው ‘Mic’d Up’ ፕሮግራም ላይ የቀረቡት የፕሮፌሽናል ጨዋታ ዳኞች ማህበር አለቃ ሀዋርድ ዌብ ውሳኔውን  ደግፈውታል።

ሀዋርድ ዌብ እንደሚሉት”ግብ ጠባቂው በግልጽ ተይዞ ስራውን እንዳይሰራ ከተደረገ ጥፋት መሆኑ አያጠራጥርም። እዚህ ጋር የታየው ተራ ንክኪ ሳይሆን፣ የዌስትሃሙ ተጫዋች ፓብሎ የአርሰናሉን ግብ ጠባቂ ዴቪድ ራያን ግራ እጅ ይዞ ዝቅ በማድረግ ኳሱን እንዳይይዝ ማድረጉ ነው። ይህ ደግሞ በቪኤአር መነጽር ግልጽ እና ግልጽ የሆነ ጥፋት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ በዳኞች መካከል የነበረው የንግግር ልውውጥም ይፋ ሆኗል።

የቪኤአር ዳኛው ዳረን ኢንግላንድ ለዋናው ዳኛ እንዲህ ሲል ተሰምቷል ክሪስ፣ እዚህ ጋር ፓብሎ የራያን እጅ ይዞት ይታያል። ኳሱን እንዳይዝ ተጽዕኖ አድርጎበታል። ወደ ስክሪኑ መጥተህ ብታየው ይመከራል ሲል ተደምጧል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የዌስትሃም ተጫዋቾች በሜዳው ውስጥ በነበሩ ሌሎች ንክኪዎች ላይ ቅሬታ ቢያቀርቡም፣ ዳኛው ካቫና ግን በትሮሳርድ እና በዲክላን ራይስ በኩል የታዩት ንክኪዎች ብዙም የሚረቡ አይደሉም። ዋናው ጥፋት የተፈጸመው በግብ ጠባቂው ላይ ነው፤ ደግሞ ቀዳሚው ክስተት ነው ሲሉ ይደመጣል።

ይህ ውሳኔ የተሰጠው ከ4 ደቂቃ በላይ በፈጀ የቪኤአር ምርመራ ነበር።

ይህች ደቂቃ በአርሰናል በኩል ለዋንጫ ያላቸውን ተስፋ ያለመለመች ስትሆን፣ ለዌስትሃም ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የሚያደርጉትን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ