በሀሳብ ልዕልና የሚያምን የፖለቲካ ሥነ-ምህዳርን በማስፋት ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በመመካከርና በመደጋገፍ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

በሀሳብ ልዕልና የሚያምን የፖለቲካ ሥነ-ምህዳርን በማስፋት ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በመመካከርና በመደጋገፍ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

“ለተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥርዓትና ባህል ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና!” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክልላዊ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

በተደረገው ጉብኝትና ውይይት መደሰታቸውን የገለጹት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካዮች፤ አካታችነት ያለውን የፖለቲካ ሥነ-ምህዳር በማስፋት ለሕዝብ በሚጠቅሙ አማራጮች ላይ ተደጋግፎና ተመካክሮ ለመስራት በገዥው ፓርቲ በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

እንደክልል የተጀመሩ የመልካም አስተዳደርና የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸው፤ በክልሉ ያሉትን ጸጋዎች በመለየትና ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

አስታያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም የኑሮ ውድነትና የትራንስፖርት ዋጋ ፍትሃዊ ያለመሆን እንዲሁም የሥራ አጥ ቁጥር መብዛት የመሳሰሉ ችግሮች መፍትሄ ማግኘት እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡

በቀድሞው ክልል የነበሩ የንብረት ክፍፍል ሁኔታዎች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የክፍፍል ሁኔታው ፍትሃዊ ስለመሆኑም የጋራ ም/ቤት ተወካዮች አንስተዋል፡፡

ከግል ስሜት በመውጣት ለሀገር የሚጠቅሙ ሀሳቦችን ይዞ ለውይይት መቅረብ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጠናከር ፋይዳው የላቀ ነው ያሉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

ሀገር የሚመራው ከየአቅጣጫው የሚነሱ ሀሳቦች ተደራጅተውና ተቀናጅተው ለሕዝቦች በሚጠቅም መልኩ ተሰንደው ተግባር ላይ ሲውሉ ነው ብለዋል አቶ ማስረሻ፡፡

ከመልካም አስተዳደርና ከጸጥታ ችግሮች ጋር ተያይዞ ለተነሱ ሃሳቦች ተገቢ ምላሽ በመስጠት የብልጽግናን ጉዞ ለማሳካት በላቀ ቁርጠኝነት መምራት ተገቢ መሆኑን ነው አቶ ማስረሻ የገለጹት፡፡

የሀሳብ ነጻነትንና የሕግ የበላይነትን በማስከበር በሕዝቦች መካከል መከባበርና ወንድማማችነት እንዲሰፍን ይሰራል ያሉት በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ፤ ሂደቱን እየፈተሽን የጋራ ም/ቤቱ እንዲጠናከር ይደረጋል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ይሁንታን ለማግኘት በመደማመጥና በመመካከር እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ነጋ፤ ለሕዝቦች ጥያቄ ፍትሃዊ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል፡፡

ያሳለፍናቸው ውጣውረዶች በርካታ ናቸው ያሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፤ በሀሳብ ልዕልና የሚያምን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ተቋቁሞ እየሰራ ስለሆነ ፅንፈኝነትንና አክራርነትን በመተው የተያዘው የልማት ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ቱባ ባህሎች ልማት ላይ እንዲውሉና ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በጋራ መሰራት አለበት ያሉት አቶ ሰለሞን፤ የተጀመሩ ክልላዊ የልማት ድርጅቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የውይይቱ ድባብ ለሀገር ፍቅር፣ ለልማት ካለ መሻትና መነሳሳት የመነጨ፣ ለጋራ ዕድገትና ለሕዝቦች ተጠቃሚነት ተመካክሮና ተደጋግፎ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ያመላከተ በመሆኑ ይህንን አዲስ የፖለቲካ እሳቤና ባህል ለትውልድ ለማስተላለፍ በትጋት መሰራት እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት በሕገመንግስቱ የተቀመጡ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፍትሃዊ የሐብት ክፍፍል፣ የፖለቲካ አካታችነት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሰላማዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን መርህ ያደረጉ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሕዝብ እርካታን የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው ይሰራሉ ብለዋል።

የወቅቱ ንግድ ፉክክር፣ የዓለም ፖለቲካ ጫና፣ ጦርነት፣ ከውጭ የሚደረጉ የብድር ድጋፍ መቀነስ የመሣሰሉ ጉዳዮች ተደማምረው ለኑሮ ውድነትና ለዋጋ ንረት በር የከፈቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ እንደሀገረ ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ምርቶች መተካት፣ ኢንቨስትመንትን ማበረታታትና የመሳሰሉ ስራዎች ተጠናክረው ይሰራሉ ብለዋል።

በአንጻራዊነት የተገኘውን የሰላምና የጸጥታ ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች መልካም ተሞክሮዎችን በመጋራት የሕዝቦችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የጋራ ም/ቤቱ ድርሻውን እንዲወጣ ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን