በበቆሎ አምራች አከባቢዎች እየተተገበረ የሚገኘው የኩታ ገጠም እርሻ የአርሶ አደሩን ምርታማነቱን እያረጋገጠ መሆኑ ተገለጸ

በበቆሎ አምራች አከባቢዎች እየተተገበረ የሚገኘው የኩታ ገጠም እርሻ የአርሶ አደሩን ምርታማነቱን እያረጋገጠ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ በበቆሎ አምራች አከባቢዎች እየተተገበረ የሚገኘው የኩታ ገጠም እርሻ የአርሶ አደሩን ምርታማነቱን እያረጋገጠ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

በርዕሰ አስተዳደሩ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በጋሞ ዞን በደረማሎ ወረዳ በልግ እርሻን ጎብኝተዋል።

በክልሉ በበቆሎ አምራች አከባቢዎች እየተተገበረ የሚገኘው የኩታ ገጠም እርሻ የአርሶ አደሩን ምርታማነቱን እያረጋገጠ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናግረዋል።

በጋሞ ዞን ደረማሎ ወረዳ በዶምኤ ቀበሌ የሚገኘውን የበቆሎ ክላስተር በጎበኙበት ወቅት ለደቡብ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት የኩታ ገጠም እርሻ የአርሶ አደሩን ምርታማነትን ከማረጋገጡ ባለፈ የአርሶ አደሮችን ማህበራዊ ትስስርን የሚያጎለብት ነው።

በይበልጥ አርሶ አደሮቹ በሰው ጉልበት ከማረስ ተላቀው በትራክተር ማረስ መጀመራቸውን ምርትና ምርታማነታቸውን እንደጨመረም ተናግረዋል።

በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች ሳይታረስ የሚያድር መሬት እንዳይኖር እየተሠራ ቆይቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በበለጠ እርሻ የታየው ውጤት ከዘር አቅርቦት ጀምሮ እስከ ተባይ መከላከል ድረስ በተቀናጀ ሁኔታ ስለመሠራቱም ያመላክታል ብለዋል።

በቀሪ የእርሻ ጊዜ ሰብልን መንከባከብና የተባይ መከላከል ስራውን አርሶ አደሩ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አፅእኖት ሰጥተዋል።

ከዘር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች በክልል ደረጃ መገምገሙን ያስታወሱት አቶ ጥላሁን ተግዳሮቱን ለመፍታት ከዘር አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

አቶ ጥላሁን አያይዘውም አምና ከክልሉ ከ62 ሺህ ቶን በላይ የሰሊጥ ምርት ወደ ውጭ የተላከ ሲሆን በዘንድሮ የተገኘውን ውጤት በማጠናከር የማሾ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።

በርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የተመራ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በደረማሎ ወረዳ ቆይታቸው የዋጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታንም ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ: በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን