የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የንግዱ ማህበረሰብ እና ባለሀብቶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የየም ዞን አስተዳደር ገለፀ

በዞኑ “የብልፅግና ጉዟችንና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና” በሚል መሪ ቃል ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በሣጃ ከተማ ዞናዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የንግዱ ማህበረሰብ እና ባለሀብቶች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል ፡፡

በመሆኑም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የንግዱ ማህበረሰብ እና ባለሀብቶች ተሳትፏቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ጤናማ የንግድ ሥርዓት እና የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር የንግዱ ማህበረሰብ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ በማንሳት የሀገር ብሎም የግል ዘርፉን ኢኮኖሚ ለማሣደግ ገቢ እና ወጪ በአግባቡ ሠርቶ በታማኝነትና ግልፀኝነት የሚሠራ ነጋዴን ለማፍራት የሁሉ ርብርብ እንደምያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የየም ዞን ብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ዝናብ በበኩላቸው በንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ፈትሾ ለማረም ፖርቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ግለሰቦች በሚሠሩት ጠንካራ ሥራ አካባቢ፣ መዋቅር እና ማህበረሰብ እንደሚያድግ ጠቁመው በመሆኑም ተባብሮ በመሥራት አብሮ ማደግ ላይ የተመሠረተ የዘመነ የንግድ ሥርዓትን በመከተል ለለውጥ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል ።

መንግስትም አሣሪ የሆኑ የንግድ ሕጎችን በመፈተሽ ለማስተካከል እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ሀላፊው ባለሀብቱን በመያዝ የሀገር ሠላምን ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ አካላት በመጠንቀቅ ለሀገር ብልፅግና መሥራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት ።

የየም ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ በዛ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት ባለፉት ሰባት ዓመታት በዞኑ 60 ባለሀብቶችን በማሠማራት ከ6ሺ 200 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ በአካባቢው የሚመረቱ ምርቶችን በአግባቡ እንዲሽጡ የሰንበት ገበያን በመጠቀም ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል ።

የጅምላ አከፋፋይ ያለመኖር፣ የደረሰኝ አጠቃቀም፣ የውሃ፣ ትራንስፓርት እና መሠል ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ።

የየም ዞን ገቢዎች ባለሥልጣን ቅ/ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ቦጋለ ዘርፉ የንግዱ ማህበረሰብ እና ባለሀብቶች ባደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ገቢ ተሰብስቦ ለልማት መዋሉን ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ የገበያ አማራጮችን በማሣደግ እና ከአዲስ አበባ ጀምሮ በየመንገዱ ያሉ ሕገ ወጥ ኬላዎች እንዲሁም ከደረሰኝ አሠጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱ ተሣታፊዎች ጠይቀዋል።

ዘጋቢ ፣ ማሙዬ ፊጣ-ከወልቂጤ ጣቢያችን