በደንባ ጎፋ ወረዳ 21 ኪ.ሜ መንገድ ተገንብቶ አገልግሎት መሥጠት ጀመረ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን ደንባ ጎፋ ወረዳ 21 ኪ.ሜ መንገድ ተገንብቶ አገልግሎት መሥጠት መጀመሩን የወረዳው አስተዳደር ገለጸ፡፡
የደንባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ አራታ የተጀመረው የትራንስፖርት አገልግሎት የህዝቡ የዘመናት ጥያቄ ሆኖ የቆየ መሆኑን አንስተው አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ህዝቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በገበያ ቀናት ወደ አራት መዳረሻዎች ስምሪት ለመስጠት ከባለድርሻዎች ጋር ከስምምነት መደረሱን አንስተው የህዝቡን ችግር የሚፈታ ስራ የሰራውን ድርጅት አመስግነዋል።
የኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የመንገድና ስራ ደህንነት ሱፐርቫይዘር አቶ እንዳለህ መሸሻ ድርጅቱ በህዝቡ ላይ የሚደርሰውን እንግልት ከግምት በማስገባት ከሚሰራው መደበኛ ተግባር በተጨማሪ ይህን አገልግሎት ሰጥቷል ብለዋል።
የጎፋ ባራንቼ የህዝብ ማመላለሻ ቦርድ ዋና ሰብሳብ አቶ ጀማል ለበኔ እና የባራንቼ የህዝብ ማመላለሻ ማህበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉነህ ጋሻው የትራንስፖርት ችግር ከሚታይባቸው አካባቢዎች በይፋ አገልግሎት ለመጀመር መሉ ዝግጅት አድርገው ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል።
ከ40 ኪ.ሜ በላይ መንገድ በጊዜያዊነት በ 300 ብር ታርፍ አገልግሎት ለመስጠት መወሰናቸውን የገለፁት ሰብሳቢው ይህ የህብረተሰቡን የኑሮ ጫና ከመቀነስ አንፃር እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ ኡጋና ዲዶ፣ ሙላቱ ሙኩሎ እና አየለ ዝግሌ የአከባቢው ነዋሪዎች ሲሆኑ ከዚህ በፊት በትራንስፖርት እጥረት የጤና፣ የትምህርት እና ለሌሎች ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ሰለባ ስሆኑ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
በድጋሚ ወደ ቀድመው ችግር ላለመግባት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ጠቁመው ችግሩን ለማቃለል የበኩላቸውን ሚና ለተጫወቱ አካላት የአከባቢው ምስጋና አቅርበዋል።
የተጀመረው አገልግሎት በጎፋ ዞን ደንባ ጎፋ ወረዳ የወይዴ ውርክ እና የላይማ ፃላ አካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
ዘጋቢ: ሲሳይ አፃ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ባለፉት አመታት የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርአትን በማዘመን የተሰሩ ስራዎች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኤጀንሲ አስታወቀ
የጤናው ዘርፍ ተግባራት በኃላፊነት እና በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ
በኮንታ ዞን የሽግግር ም/ቤት 4ኛ ዙር 4ኛ ሥራ ዘመን 26ኛው መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ