በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ሊካሄድ ነው
የወረዳው ጤና ጽ/ቤቱ በልዩ ወረዳው ግንቦት 6 እስከ 15/2017 ዓ.ም የሚሰጠውን የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብድልኸይ ኑርሀሰን በዚህ ወቅት እንደገለፁት የኩፍኝ በሽታ በቀላሉ የሚተላለፍና በጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚበረታ ከመሆኑም ባሻገር በስረዓተ ምግብ እጥረት የተጎዱ ህጻናት በበሽታው የመያዝና አልፎ አልፎም የመሞት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
በልዩ ወረዳው የክትባት ዘመቻው ግንቦት 6 እስከ 15/2017 ዓ.ም ቤት ለቤት ፣ በጤናና በትምህርት ተቋማት እንዲሁም በጊዜያዊ ጣቢያዎች ይሰጣል ያሉት አቶ አብድልኸይ ዕድሜያቸው ከ9 ወር እስከ 5 ዓመት ያሉ ከ17 ሺህ በላይ ሕፃናት ክትባቱን እንዲያገኙ ይሰራል ብለዋል፡፡
የክትባት ዘመቻው የተቀናጀና ከወትሮው በተለየ መልኩ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ተግባር መሆኑን የገለፁት ሃላፊው ከክትባት ዘመቻው ጎን ለጎንም የፖሊዮ ክትባት፣ የስረዓተ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ህፃናትን ጨምሮ የፌስቱላና የማህፀን ውልቃት ችግር ያለባቸው እናቶችን የመለየትና ሌሎችም የእናቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎት ስራዎች በንቅናቄ እንደሚሰሩም አብራርተዋል ፡፡
በመሆኑም የክትባት ዘመቻው ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አቶ አብድልኸይ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ ፡ጅላሉ ፈድሉ-ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ በ5ኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ6 መቶ ሺ በላይ ህፃናት ተጠቃሚ ይሆናሉ
በክልሉ 5ኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው በክልሉ ከ 1.1ሚሊየን በላይ ህፃናት የክትባት መርሐግብሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ
በኮንታ ዞን አመያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የእናቶች እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ