የተቀናጀ ኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህጻናትን ተደራሽ ይደረጋል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከግንቦት 06/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው የተቀናጀ ኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህጻናትን ተደራሽ እንደሚደረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ፣ የስርዓት ምግብ ልየታ እንዲሁም የእናቶችንና ህጻናት ጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያለመ የምክክር መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጂንካ ከተማ አካሂዷል።
13 አይነት መድኃኒቶችን ለ12 በሽታዎች መከላከያ ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ19 ሚሊዮን ህጻናት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህጻናት የኩፍኝና ሌሎች በሽታዎች የመከላከያ ክትባት ዘመቻ ተደራሽ የሚደረግ ስሆን እንደ ሀገር 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ለኩፍኝ በሽታ ተጋላጭ የመሆን እድል እንዳለውም ተጠቁሟል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ ከ3 ሚሊዬን በላይ ህፃናት በክትባት መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች የሚሞቱ ሲሆን ከዚህም 99 በመቶ የሚሆነው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት እንደሚከሰት ጥናቶች ይጠቁማሉ።
በሀገር አቀፍ በየወቅቱ ከሚሰጡ መከላከልን መሠረት ያደረጉ ከትባቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከግንቦት 6 እስከ 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ12ቱ ዞኖች በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ህፃናት ጤና የክትባት ክፍል አስተባባሪ አቶ አብዱልካድር ሁሴን፤ የኩፍኝ በሽታ ህፃናት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠቃ መሆኑን ገልፀው በተያዘው በጀት አመት በክልሉ በተወሰኑ ዞኖች በወረርሽኙ ተከስቶ በተደረገው የተቀናጀ ርብርብ መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል።
በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የክትባት ዘመቻ ስደረግ መቆየቱን ያመላከቱት አስተባባሪው ከግንቦት 06/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው የተቀናጀ ክትባት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ህፃናትን ተደራሽ እንደሚደረግ አመልክተዋል።
ለዚህም በሁሉም የክልሉ ዞኖች እስከ ታቸኛው መዋቅር ድረስ በቂ የግበዓት ስርጭትና የሰው ኃይል ስምሪት ተደረጓል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የፕሮግራሞች ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መና መኩሪያ እንደገለፁት፤ በክልሉ 13 አይነት መድኃኒቶችን ለ12 በሽታዎች መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥና በዚህም የህፃናትን ሞት ለመቀነስ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት እንደሚከታቡ አብራርተዋል።
ከግንቦት 06/2017 ዓ.ም ጀምሮ ከሚካሄደው የተቀናጀ ክትባት ዘመቻ ጎን ለጎን የወባና ሌሎችም በሽታዎችና በምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናት ልየታና ህክምና እንደምሰጥ የገለፁት አቶ መና ለስኬታማነቱ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት እንዲወስዱ አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ለሚካሄደው የተቀናጀ ክትባት ዘመቻ በዞናቸው በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ለስኬታማነቱ ሁሉም ማህበረሰብ አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የሣንባ በሽታንና ሌሎች ስር የሰደዱ የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ
በዳውሮ ዞን በሎማ ቦሣ ወረዳ የወባ ወረርሽን ለመከላከል የኬሚካል ርጭት እየተካደ ነው
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ገለፀ