የሣንባ በሽታንና ሌሎች ስር የሰደዱ የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ

የሣንባ በሽታንና ሌሎች ስር የሰደዱ የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ

ቢሮው “ላብ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ” ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በቲቢና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ችግሮች ልየታ ላይ ከ4 ዞኖች ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና በአርባ ምንጭ ከተማ ሰጥቷል።

የህብረተሰቡ የጤና ችግር ሆኖ የቆየና አሁንም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን እያሰቃየ ያለውን የቲቢ በሽታ አስተላላፊ ባክቴሪያ ያለባቸውን ለመለየት ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን የሚናገሩት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ቲቢ፣ ሥጋ ደዌ እና ሌሎች የሳንባ በሽታዎች ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታዲዎስ ጤና፤ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ77 በላይ ዘመናዊ የቲቢ መመርመሪያ ማሽኖች በክልሉ መኖራቸውን የሚናገሩት አስተባባሪው፤ ከ6 በላይ ማሽኖች በጎፋ፣ ኮንሶ፣ ቡርጂና ኮሬ ዞኖች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከሥልጠናው በኋላ በርካታ የቲቢ በሽተኞች ተለይተው ተገቢውን የህክምና አግልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋልም ብለዋል አስተባባሪው።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪና የላብ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ዳልቦ፤ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የሳንባ በሽታ ህመምተኞችንና የመተንፈሻ አካላት ችግሮች ተጠቂ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመለየት ከህክምና ጋር የማገናኘት ሥራን ለመሥራት የሚያስችል የክህሎት ማሳደጊያ ሥራዎች ላይ ፕሮጀክቱ በዋናነት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም በ4ቱ ዞኖች 90 ለሚሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሥልጠናው መሰጠቱን ጠቁመው አሁን ደግሞ ለ80 ጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን አስረድተዋል።

ከ 1 ሺህ 500 በላይ የሳንባ ነቀርሳ ሕሙማን ፣ 600 ስር የሰደዱ መተንፈሻ አካላት ችግር እና ከአንድ ሺህ በላይ የአስም በሽታ ያለባቸውን ወገኖችን ለመለየት ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ ዳልቦ፤ በአንድ አመት ውስጥ አፈፃፀሙ ከ95 ከመቶ በላይ ለማድረስ በአፅኖት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በስልጠናው ከጎፋ፣ ኮንሶ፣ ቡርጂና ኮሬ ዞኖች የተውጣጡ ባለሙያዎች በተግባር ተኮር የታገዘ ስልጠና በማግኘታቸው ክህሎታቸው እንዳደገ የሚናገሩት ደግሞ ወ/ሮ ምስራቅ መቆያ እና አቶ ሰለሞን ቸርነት ናቸው።

ዘጋቢ፡ አበበ ዳባ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን