በምርጥ ዘር ብዜት ሥራ አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው – የኣሪ ዞን አስተዳደር
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተጀመረው የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ የዘር ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለመጨመር እየተሠራ ነው ሲል የኣሪ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
የኣሪ ዞን የሥራ ኃላፊዎች በደቡብ ኣሪ ወረዳ ጨለጎድ ቀበሌ በ1መቶ 8 ኼክታር መሬት እየለማ ያለውን የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ምልከታ አድርገዋል።
ምርታማነትን ከሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች አንዱ ሲሆን ከዚህ ቀደም በኣሪ ዞን ከፍተኛ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ያለመ በዞኑ እንደየአካባቢው ሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች እየለሙ እንደሚገኝ የኣሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ደቡብ ኣሪ ወረዳ ጨለጎድ ቀበሌ እየለማ ያለው የቢኤች 40 በቆሎ ዘር ለቀጣይ ለዞኑ ተስፋ ሰጭ ነውም ብለዋል።
በዞኑ በተያዘው የበልግ ምርት ዘመን የምርጥ ዘር ብዜትን ጨምሮ በሁሉም የሰብል ዓይነት 48ሺህ 1መቶ 90 ኼክታር መሬት እየለማ እንደምገኝ አስታውቀዋል።
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸው፤ በዞኑ በምርጥ ዘር ብዜት የተጀመረው ሥራ የዞኑን ምርጥ ዘር ፍላጎት ባለፈ ዘርፉ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲያሳድግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዞኑ ባሉ አራቱም ወረዳዎች ከአካባቢው ሥነ ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆኑ የግብርና ምርቶችን በማላመድ የአርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃምነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
አሁን ላይ በወረዳው በምርጥ ዘር ብዜት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር የመፍጠርና ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጡ ለማስቻል እየተሠራ እንዳለ የደቡብ ኣሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛው ኃይሌ አመላክተዋል።
በበቆሎ ዘር ብዜት የተሠማሩ አርሶ አደሮችም በቡቃያ ደረጃ ያለው ምርት ተስፋ ሰጭ መሆኑን አመላክተው ለዚህ ስኬት የግበዓትና ሙያዊ ድጋፍ ያደረጉ የመንግስት አካላትን አመስግነዋል።
ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ
በቴክኖሎጂ የታገዘ መንግሥት የግዥ ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የሀብት ብክነትን መቀነስ ይገባል – ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
በክልሉ የሚመረቱ የግብርና ውጤቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለማገበያየት የሚያስችል ኢንዱስትሪ ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ