በክልሉ የሚመረቱ የግብርና ውጤቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለማገበያየት የሚያስችል ኢንዱስትሪ ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ
የክልሉ 3ኛ ዙር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በማሳደግ ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካትና ወደ ውጭ ለመላክ እየተደረገ ያለውን ጥረት ውጤታማ እያደረገ ነው ብለዋል።
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እየተመረቱ ያሉ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ከአካባቢ አልፎ በሀገር ደረጃና በውጭ ገበያ እንዲገበያዩ ማስቻል ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በመሆኑም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ የሚያስችሉ የመንገድ፣ የውሃ፣ የኃይልና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት በዘርፉ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በክልሉ ውስጥ ካሉ 750 ያህል ኢንዱስትሪዎች ውስጥ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ከ20 በመቶ የማይበልጥ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ጠቅሰዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው ጋግያብ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ340 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም ከ6ሺህ ለሚበልጡ ሥራ አጦች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በመትከል ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሠራ መጠቆማቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ዘርፉ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ገልጸዋል።
በዞኑ በቂ የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች መኖራቸውን ገልጸው ለአምራቾች የመሸጫ ቦታ በማዘጋጀት የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየሠራን ነው ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
More Stories
በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ
በቴክኖሎጂ የታገዘ መንግሥት የግዥ ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የሀብት ብክነትን መቀነስ ይገባል – ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
በምርጥ ዘር ብዜት ሥራ አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው – የኣሪ ዞን አስተዳደር