ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ግብዓቶች አጠቃቀም ማሻሻልና ማዘመን እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ግብዓቶች አጠቃቀም ማሻሻልና ማዘመን እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

በልዩ ወረዳው የ2017/18 ምርት ዘመን ከ9ሺህ 70 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ የበልግ ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች የ2017/18 ምርት ዘመን የበልግ እርሻ ተግባር ለማሳካት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የምርት ዘመኑን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ማሳን ደጋግሞ ማረስ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ማሳቸውን እስከ አራተኛ ዙር በማረስ በበልግ እርሻ ለዘር ማዘጋጀታቸውን ያነጋገርናቸው የፈርዛኖ እና የባችራ ቀበሌ አርሶ አደሮች ገልፀዋል።

የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ገዝተው ማሳቸውን በተለያዩ የበልግ ሰብሎች በዘር ለመሸፈን ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ማርቆስ ዱጤቦ እና ማርቆስ ሲግሶ ተናግረዋል።

አንዳንድ የሰሜን አምቡኩና ቀበሌ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፤ ጥንቅሩን የጠበቀ የግብርና ግብዓቶች ተጠቅመው ማሳቸውን በዘር ለመሸፈን እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የበልግ እርሻ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ያላገናዘበ መሆኑን የተናገሩት አርሶ አደሮቹ ከምግብ ዋስትና ችግሮች ለመላቀቅ በተቻለ መጠን የኢኮኖሚ ጫና በመቋቋም የግብርና ግብዓቶች አጠቃቀም ማሻሻልና ማዘመን እንደሚገባም ገልፀዋል።

በባችራ ቀበሌ የ2017/18 ምርት ዘመን የበልግ እርሻ ተግባር ለማሳካት ተገቢውን የማሳ ዝግጅት ከማድረግ ባሻገር የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እጅ በእጅ በመግዛት በቀበሌው ከ5 መቶ 50 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ የበልግ ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን የቀበሌው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ታዲዎስ ብርሃኑ ተናግረዋል።

በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት እርሻ ዘርፍ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ታምራት ፉንድሶ እንደገለጹት፤ የ2017/18 ምርት ዘመን የበልግ እርሻ ስራ ለማሳካት መጠነ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

በዚህም 9ሺህ 72 ሄክታር ማሳ በተለያዩ የበልግ ሰብሎች በዘር ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑንም አቶ ታምራት አስታውቀዋል።

በበልግ እርሻው 8ሺህ 9 መቶ 36 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና 3ሺህ 75 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር በተቀመጠለት የዋጋ ዝርዝር መሰረት ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት መታቀዱንም አቶ ታምራት ጠቁመዋል።

በእስካሁኑ ሂደት 3ሺህ 70 ሄክታር ማሳ በዘር መሸፈኑን የተናገሩት ቡድን መሪው፥ 1ሺህ 6 መቶ 72 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና 20 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉን አመላክተዋል።

ዘጋቢ: ጡሚሶ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን