ፍሎር ፕሮጀክቱ (FLOUR project) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ኮቾሬ፣ ወናጎ እና ይርጋጨፌ ወረዳ የቡና ልማት እና ጥራት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ለአርሶ አደሮች፣ ለግብርና ባለሙያዎች እና ለባለድርሻ አካላት ነው የተሰጠው።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የይርጋጨፌ ወረዳ አካባቢ ጥበቃ እና ደን ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጴጥሮስ ሎሌ፤ ቡና ፍሬያማነቱ እንዲጨምር በኩታ ገጠም ማልማት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ቡና የውጭ ገቢ ምንጭ ስለሆነ አርሶ አደሮች ባለ ልዩ ጣዕም ቡና እንዲያመርቱ በተግባር እና በጽንስ ሀሳብ ስልጠና መሰጠቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍሎር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አለምበጁ ክፍሌ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ጥራቱን የጠበቀ ቡና አርሶ አደሩ ለገበያ እንዲያቀርብ እና በአለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው፤ ይህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ቡናና ቅመማ ቅመም ልማት እና ግብይት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበራ አሰፋ፤ ፍሎር ፕሮጀክት በወረዳው አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አንስተው ወረዳውም ፍሎር ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ያገኙት ስልጠና ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው የገለጹት የስልጠናው ተሳታፊ አርሶ አደር ሽፈራው ተጫነው፣ ወርቅዬ ሻሎ እና ሌሎችም በተግባር ላይ ለማዋል ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ዘጋቢ: አሀዱ አሸናፊ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የትምህርት ቤቶችን የውስጥ ገቢ ማሳደግ ለትምህርት የልማት ዘርፍ ሥራዎች አጋዥ መሆኑ ተገለጸ
ትምህርት የሀገርን ኢኮኖሚ ከመገንባት ባለፈ በራስ የሚተማመን ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተገለጸ
ከልጅነቴ ጀምሮ የግብርና ሥራ ሱሴ ነው ! ማሳዬን በቀን ሦስት፣ አራት ጊዜ ካልጎበኘሁኝ ያመኛል – ሞዴል አርሶአደር አቶ ኮቾ ከተማ