ትምህርት የሀገርን ኢኮኖሚ ከመገንባት ባለፈ በራስ የሚተማመን ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተገለጸ

ትምህርት የሀገርን ኢኮኖሚ ከመገንባት ባለፈ በራስ የሚተማመን ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 11/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ትምህርት የሀገርን ኢኮኖሚ ከመገንባት ባለፈ በራስ የሚተማመን ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያስችል የዳሞት ወይዴ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ገለጸ፡፡

በዳሞት ወይዴ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት የ2018 ትምህርት ዘመን የእስካሁን አፈጻጸምና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የዳሞት ወይዴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ ቶማ ትምህርት የሀገራችን ኢኮኖሚ ከመገንባት ባለፈ በራስ የሚተማመን ዜጋን ለመፍጠርና የፈጠራ ክህሎትን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና መኖሩን አመላክተዋል።

ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትምህርት ዋነኛ መሳሪያ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪ የትምህርት ስብራትን በዘላቂነት ለመጠገንና የተማሪዎቻችን ውጤት ለማሻሻል እንዲሁም ከወደቅንበት ደንግጠን ለመነሳት የትምህርት አመራር፣ ባለሙያዎች እና ህብረተሰቡ በጋራ በመቀናጀት ለውጤታማነቱ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል።

የትምህርት ሥራን ለማሳለጥ የሚስተዋለውን የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የወረዳ አስተዳዳሩ አቅም የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው÷ አመራሩ የትምህርት ዘርፍ ስራን ከመደበኛው ሥራ ጋር በእኩል እንዲደግፉና እንዲከታተሉ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አሳስበዋል።

የዳሞት ወይዴ ወረዳ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ መርክነህ ኤቼ በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የህብረተሰብ እና የባለድርሻዎች ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በየዓመቱ እየተሽቆለቆለ የሚመጣውን የተማሪዎችን ውጤት ከፍ ለማድረግና የትምህርት ጥራት ለመጠበቅ የትምህርት አመራሩና ባለሙያዎች ከወትሮ በበለጠ ለመስራት ቁርጠኛ አቋም መያዝ እንዳለባቸው የመንግሥት ዋና ተጠሪ አስታውቀዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የትምህርት ስራን ውጤታማ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ይሰጣል ያሉት የመንግሥት ዋና ተጠሪ የትምህርት ስርዓቱ በሚፈለገው ልክ ውጤት ለማምጣት በቀጣይ ጊዜያት ትምህርት ቤቶችን የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል።

የዳሞት ወይዴ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምትኩ ኮቻሬ እንደተናገሩት የትምህርት ስራ ለትምህርት አመራር ብቻ ሰጥተን የምንተው ሳይሆን የሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች በቁጭት ተነስተው በውሳኔ የሚሳተፉበትና የሚተገብሩበት ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የትምህርት አመራር ሚና የጎላ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ምትኩ ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች የሚሰጠው የትምህርት አሰጣጥ ትክክለኛነቱን በቅርበት በመከታተል የተሻለውን ውጤት እንዲያስመዝግቡ የማድረግ ስራ በዕቅድ መመራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመድረኩም የወረዳው አሰተባባሪ አካላትና አጠቃላይ መካከለኛ አመራሮች፣የቀበሌ ዋና አስተዳዳሪዎች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ ርዕሳነ-መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ይትባረክ ጎኣ – ከዋካ ጣቢያችን