ሀዋሳ፡ ሕዳር 11/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትምህርት ቤቶችን የውስጥ ገቢ ማሳደግ ለትምህርት የልማት ዘርፍ አጋዥ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምሀርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ገለጹ፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች በዳውሮ ዞን የዋካ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት በአካል ተገኝተው ጎበኝተዋል።
የቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ እንደገለጹት የትምህርት ልማት ሥራዎችን ለማሳደግ የት/ቤት የውስጥ ገቢ ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመው÷ እንደ ሀገር የተቀመጠውን ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ዓላማ ለማሳካት ክልሉ በትምህርት ቤቶች የልማት ስራዎች ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ የቢሮ ኃላፊው ከትምህርት ቤት ኃላፊዎችና መምህራን ጋር የጋራ ውይይት አድርገዋል።
በውይይት ወቅትም ከመምህራን የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በዋናነት በደመወዝ እና ጥቅማጥቅም ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶች በትምህርት ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ከትምህርቱ ቤቱ መምህራን መካከል መምህር ሠላም ተስፋዬና ወርቁ ወላንቾ አንስተዋል።
በተጨማሪም የመምህራን ደረጃ ዕድገትና የእርከን ውዝፍ ክፍያ በተመለከተ ያልተመለሰ ጥያቄ መሆኑን በማስረዳት ችግሮቹ መቀረፍ እንደሚገባቸውም መምህራኑ ጠይቀዋል።
የቢሮ ኃላፊው ከመምህራንና ከትምህት ቤት ኃላፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለቀጣይ ክልሉ ወስዶ የሚያከናውናቸው በርካታ የቤት ሥራዎች መኖራቸውንም ጠቁመው÷ እነዚህን የተስተዋሉ ችግሮችን ከመቅረፍ በተጨማሪ በትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢ ለማሳደግ የልማት ሥራ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ሁሉም በጋራ ተጋግዞ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በጉብኝቱ ላይ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን፣ የዞኑ ትምህርት መምሪያ የሥራ ሂደት አስተባባሪዎችን ጨምሮ የዋካ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ናቸው።
ዘጋቢ፡ አፈወርቅ ኦሹ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
ትምህርት የሀገርን ኢኮኖሚ ከመገንባት ባለፈ በራስ የሚተማመን ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተገለጸ
ከልጅነቴ ጀምሮ የግብርና ሥራ ሱሴ ነው ! ማሳዬን በቀን ሦስት፣ አራት ጊዜ ካልጎበኘሁኝ ያመኛል – ሞዴል አርሶአደር አቶ ኮቾ ከተማ
የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ዙር የከፍተኛና መካከለኛ የአመራሮች ስልጠና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መሰጠት ጀመረ